በግድቡ ላይ ያሳየነውን አንድነት በሌሎች ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ እንደግመዋለን ሲሉ የክልሉ ነዋሪዎች ተናገሩ

Spread the love

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያደረግነውን የተጠናከረ ድጋፍ በሌሎች ትላልቅ ልማቶች ላይም ለመድገም የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

“በሕብረት ችለናል” በሚል መሪ ሀሳብ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃን በማስመልከት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በቦንጋ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡

ከዳዉሮ ዞን የመጡት አቶ በለጠ ባሹ በሰጡት አስተያየት

የሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ ትግል በማድረግ ትልቅ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን እና በቀጣይ ከመንግሥታችን ጎን በመሆን ለልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች የሚጠበቅብንን አስተዋፅኦ ማበርከት አለብን ብለዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ከተሳተፉት መካከል የቦንጋ ነዋሪ አቶ ማቹሎ መኩሪያ በሰጡት አስተያየት የሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ በጋራ ተቀናጅተን መልማት እንደምንችል ማሳያ መሆኑን አመልክተው ደስታቸውን ለመግለጽ በማለዳው ወደ ሰልፋ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በተፈጥሮ የተሰጠንን ሀብት በራሳችን አቅም እና ሀብት የገነባነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገራችንን አንድነት የሚያጠናክርና የሚያኮራ መሆኑን ጠቅሰው የሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ያደረግነውን የተጠናከረ ድጋፍ በሌሎች ልማቶች ላይ ለመድገም የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አባይነሽ አበበ፤ ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት እና በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ አስታውሰው፤ ግድቡ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ በስኬት በመጠናቀቁ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ግድቡ ሁሉንም ማህበረሰብ በአንድነት ያስተሳሰረ የህልውናችን መሠረት በመሆኑ ለፍጻሜ በመድረሱ ልዩ ደስታ እንደተሰማቸውና በየአካባቢው በተጀመሩ የልማት ስራዎች ሁሉ በመሳተፍ ሀገራቸውን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማድረስ እንደሚተጉም ተናግረዋል።

ሌላኛ የሰልፉ ተሳታፊ ምክትል ኮማንደር እንዳለ ዓለሙ በበኩላቸው ግድቡ ለፍጻሜ እንዲደርስ ምኞታቸው በመሆኑ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውንና በዚህም ኩራት እንደሚሰማቸው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያውያን በአንድነቅ ከቆምን፣ የልማት እቅዶቻችንን ማሳካት እንደምንችል ግድቡ ትልቅ ማስረጃ ነው በማለት የተናገሩት አቶ አደመ አበበ ናቸው።

ግድቡ ለሀገራችን ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እና በቀጣይ ሀገራችን የባህር በር እንድታገኝ የተጠናከረ የዲፒሎማሲ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባትም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል ።

በካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *