




ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያዊያን ተባብረው በላብና በደማቸው ያፀኑት የወል ቅርስ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅን አስመልከተው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ በቦንጋ ከተማ የተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በተለያዩ ትዕይንቶች ታጅቦ በስኬት ተጠናቋል።
በህዝባዊ ሰልፉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ግድቡ መላው ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ያስተሳሰረ የወል ቅርስ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በራሷው ሀብት እንዳትጠቀም ስደረግባት የነበረው ውስጣዊና ውጫዊ ጫና በመቋቋም በአለም አደባባይ እንደሚትችል አስመስክራለችም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።
በግድቡ የተገኘው ስኬት መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ ለጀመረው ጥረት ተጨማሪ አቅም የፈጠረ መኾኑንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠቆሙት።
ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር የህዝባችንን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት የቀጣዩ ትኩረት መኾን እንደሚገባ ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጅነር ነጋሽ ለሌሎች ተደማሪ ድሎች ለመቀዳጀት በኅብር መቆምና መጽናት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝቦች በግድቡ ግንባታ ወቅት በተለያየ መልኩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና መስዕዋትነት ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ አከባቢንና ሀገር ለመቀየር ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት በቁርጠኝነት መስራት አለበት ብለዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው የዞኑ ህዝብ ባለፋት የግድቡ ግንባታ ወቅት የዞኑ ህዝብና መንግሥት ከ143 ሚሊዮን በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
