




የሚቀርቡ ጥያቄዎች ሕጎችንና አሰራሮችን በመከተል ወንድማማችነትና አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ ሕገ መንግሥታዊ ምላሽ እየሰጡ መሄድ ተጠናክሮ አንደሚቀጥል የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰን የሰላም ግንባታ ቋሚ ጸሐፊ የተከበሩ አቶ ፍቅሬ አማን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ቋሚ ኮሚቴው በበጀት ዓመቱ በርካታ አንኳር ጉዳዮችን ማከናወኑን በዋናነትም ከግጭት መከላከልና ከሰላም ግንባታ አንጻር በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ስር እንዲሰድ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራርም ትኩረት ሰጥቶ መሥራትን ጨምሮ በህዝበ ውሳኔ የምርጫ ስርዓት መሰረት ራሳቸውን መልሰው ያደራጁ አዳዲስ ክልሎች በውስጣቸው በሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል ህብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ መድረክ በማዘጋጀት የተሳካ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ከሚመለከታቸው የቀርቡ አቤቱታዎች በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት፣ በአዋጅ ቁጥር 1261/2013 እንዲሁም በደንብ ቁጥር 3 አማካኝነት ጥናቶችን በማድረግ ሕገመንግሥታዊ ምላሽ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ትኩረቱ እንደነበር የጠቀሱት የተከበሩ አቶ ፍቅሬ እስከ ክልል ጭምር በመሄድ የድጋፍና ክትትል ሥራ በማጠናከር ወደ ምክር ቤቱ የሚመጡ አቤቱታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጥላሁን ከበደ ቋሚ ኮሚቴው ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ሕገ መንግሥቱንና ሌሎችን አሠራሮች በመከተል ሕገ መንግሥታዊ ምላሽ እንዲያገኙ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ የውሳኔ ሃሳቦችን ለም/ቤቱ በማቅረብ እያስወሰነ ሲሠራ መቆየቱን በማስታወስ በቀጣይም የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ሕጎችንና አሠራሮች በመከተል ወንድማማችነትንና አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ ሕገ መንግሥታዊ ምላሽ እየሰጡ መሄድ እንዲሁም ከግጭት መከላከልና ከሰላም ዕሴት ግንባታ አንጻር ከሚመለከተው ጋር ተቀናጅቶ መሥራት የቋሚ ኮሚቴው ትኩረት እንደሚሆን ገልፀው የቋሚ ኮሚቴውን ያለፈውን መደበኛ ቃለ ጉባዔ እና የዕለቱን የመወያያ አጀንዳዎች በማጸደቅ ውይይቱን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
የ2017 በጀት ዓመት አፈጻፀም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ በዝርዝር ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሄዷል፡፡ ሪፖርቱና ዕቅዱ ለተከበረው ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንደሚጸደቅ ይጠበቃል፡፡
የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 62፣48 እና 39 እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በድጋሚ ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1261/2013 መሰረት የሕዝቦች ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ ምላሽ እንዲያገኝ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ የውሳኔ ሃሳቦችን ለም/ቤቱ እንደሚያቀርብ ይታወቃል::
