




ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል፣ ውጤታማ የፊስካል ሽግግርና በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገትን ማረጋገጥ ለጠንካራ የፌዴራል ሥርዓት ጽኑ መሠረቶች መሆናቸውን በኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡
የተከበሩ አቶ አሻድሊ ይህን ያሉት በ6ኛው የፓርላማ ዘመን፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 1ኛ መደበኛ ጉባኤ በሚቀርቡ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳቦች ላይ ቋሚ ኮሚቴው በመከረበት መድረክ ሲሆን ፌዴራላዊ ሥርዓት ከሌሎች ሥርዓተ መንግሥታት በተሻለ ደረጃ የሕዝቦችን በጋራና በፍትሐዊነት የመበልፀግ ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል ሥርዓት እንደሆነ ጠቁመው ለሥርዓቱ ዘላቂነት ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍልንና ውጤታማ የፊስካል ሽግግርን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የተከበሩ ምክትል ሰብሳቢው አያይዘውም በ2017 በጀት ዓመት የበይነ መንግሥታት የፊስካል ሽግግሮችን በፍሐዊነትና በውጤታማነት ለማስፈጸም የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥራ ለማከናወን፣ የድጎማና የጋራ ገቢዎች አስተዳደርና የማከፋፈያ ቀመር አተገባበርን ለመደገፍ፣ የፌዴራል የመሠረተ ልማት አውታሮች ሥርጭትን ፍትሐዊነትና ውጤታማነት አስመልክቶ ክትትል ለማድረግና ሌሎች አንኳር ጉዳዮችን አቅዶ ወደ ሥራ እንደገባ አስታውሰዋል።
ለውጡን ተከትሎ በተረገው ማሻሻያ የክልል መንግሥታት ድርሻ በ2012 በጀት ዓመት 4.2 ቢለዮን ብር ብቻ የነበረው በ2017 በጀት ዓመት 91.73 ቢሊዮን ብር ማደጉን አብራርተዋል፡፡
ጥቅል ዓላማ ያለው የድጎማ በጀት ቀመር ለማሻሻል በሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ላይ በሚገባ መሥራት የ2018 በጀት ዓመት ዋናው የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ መጥቀሳቸውን ከፓርላማ ያገኘነው መረጃ ከመላክቷል።
መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት በተለያዩ ቻናሎች ወደ ክልል መንግሥታት የሚደረጉ የፊስካል ሽግግሮችና የፌዴራል የመሠረተ ልማት ስርጭቶች በተዘረጋው አሠራር መሠረት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ሌሎች ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት እንደሆኑ አመላክተዋል::
የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በዛሬው ውሎው የቋሚ ኮሚቴው ፀሐፊ የተከበሩ አቶ ኃይሉ ኢፋ ባቀረቡት በ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ እቅድ ላይ የተወያየ ሲሆን በቀጣይ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ አቅርቦ እንደሚያስጸድቅ ይጠበቃል፡
