

”በመደመር መንግስት እይታ ለዘርፎች እምርታ’ በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 2ኛ ዙር ሀገር ዓቀፍ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በቦንጋ ከተማ ስልጠና እየወሰዱ መቆየታቸው ይታወቃል።
በቦንጋ ከተማ ስልጠና እየወሰዱ ያሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ከስልጠናዉ ጎን ለጎን ልምድ ልውውጥና ተሞክሮ መቀመር ላይ ትኩረት ያደረገ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ጉብኝት በካፋ ዞን እያደረጉ ይገኛሉ።
አመራሮቹ በክልሉ ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የቦንጋ ክላስተር ማምረቻ ማዕከል፣ ጊዲ እንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ ፣ ዲንቻ የመንግስት ሻይ ችግኝ ብዜት ጣቢያ ጉብኝት አድርገዋል።
የቦንጋ ክላስተር ማምረቻ ማዕከል አመራሮቹ የጎበኙ ሲሆን ፤ ማዕከሉ አግሮ ፕሮሰሲንግ እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያለውና በውስጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ለ336 ዜጎች በቋሚና በጊዜያዊነት የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
በማዕከሉ እንጨትና ብረታብረት ውጤቶች፣ዳቦና እንጀራ ማቀነባበሪያ፣ መጋገሪያና ማከፋፈያ፣ ቅመማ ቅመምና ማር ማቀነባበሪያ እና ብሎኬት የማምሬቻና ማከፋፈያ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ በምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በጀት ድጋፍ የተቋቋመው ዲንቻ የመንግስት ሻይ ችግኝ ብዜት ጣቢያ ሌላኛው የልማት ጉብኝት አካል ነው።
በዲንቻ የመንግስት ሻይ ችግኝ ጣቢያው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚገኙም በጉብኝቱ ወቅት በተደረገው ማብራሪያ ማረጋገጥ ተችሏል።
በተጨማሪም ጊዲ የእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ ሰልጠኝ አመራሮች ምልከታ ያደረጉ ሲሆኑ ማዕከሉ 81 አባላትን የያዘ 16 ማህበራት ተደራጅተው በዞኑ እና ከተማ አስተዳደር በጀት የተሰራ ሼድ ላይ በመግባት የዶሮ እርባታ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው
ለተደራጁ ማህበራት ከ4 ሺህ 4 መቶ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን የክልሉ ግብርና ቢሮ ድጋፍ ማድረጉ የተጠቀሰ ሲሆን የተለያዩ ወጣቶች በእርባታው ተሰማርተዋል።
በፍቅር ከበደ
