በክልሉ የበዓል ፍጆታ እቃዎች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት እየተሰራ ነው

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በዓላትን ተከትሎ የሚከሰቱ የምርቶችን ዋጋ ጭማሪ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ፡፡

የቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ መጪዎቹን የገናና ጥምቀት በዓላትን ተከትሎ በምርቶች ላይ እጥረትና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ለዚህም ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ግብረ ኃይል መቋቋሙን አመልክተዋል፡፡

በተለይም ግንዛቤ በመፍጠር ከበዓላት ጋር ተያይዞ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር እና የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ለበዓል አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች በብዛት ወደ ገበያዎች ከአምራቾችና ከአቅራቢዎች በስፋት እንዲቀርብና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር እየተደርገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሁሉም የአስተዳደር እርከን የበዓል ገበያዎችን የማረጋጋት ሥራ እየተከናወነ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲሸምትና የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን እንዲጠቁም ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በየደረጃው ያሉ የሕብረት ሥራ ዩኒየኖችና መሰረታዊ ማሕበራት ለበዓል ገበያ ተፈላጊ ምርቶችን በተለይም ጤፍ፣ ሽንኩርት፣ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ቅቤ፣ ቲማቲም፣ የእርድ እንስሳት፣ ፍራፍሬና ሌሎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እያደረጉ ነው ብለዋል ሲል ኤፍ ኤም ሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *