




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የጤና ቢሮ ከክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ሀገር አቀፍ የ4ኛ ዙር የፖሊዮ ዘመቻ አፈጻጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር የግምገማ መድረክ በቦንጋ አካሂደዋል።
በመድኩ ላይ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እና ሌሎች የተቀናጀ የጤና ተግባራት አፈጻጸም ሰነድ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
4ኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ከ630ሺ በላይ ህፃናት ተደራሽ መሆን መቻሉን እና 954 ሺህ በላይ ቤቶች በወቅቱ ጉብኝት መደረጉን በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በወባ ወረርሽኝ፣ በማዐጤመ አፈጻጸም፣ በወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር፣ በማርቨርግ ቫይረስ አሰሳና ቅኝት እንዲሁም በሌሎች ተግባራት ላይ በቅንጅትና በቁርጠኝነት በመስራት ለላቀ አፈጻጸም መትጋት እንደሚገባ ውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።
መድረኩን ያጠቃለሉት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃፊው አቶ ኢብራሂም ተማም ለህብረተሰቡ በፖሊዮ ዘመቻ መልክ ተደራሽ የተደረገውን ስኬቶች በአጠቃላይ በጤናው ዘርፍ በተለይ በመደበኛ ክትባት ስራዎች ላይ አጠናክሮ ለማስቀጠል የቤት ስራ መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በወባ መከላከልና መቆጣጠር ሂደት ግንዛቤ ከመፍጠር፣ አካባቢውን ከማጽዳት፣ የአጎበር አጠቃቀምና ሌሎች ጥንቃቄዎች በመወሰድ የወባ ጫና ባለባቸው ወረዳዎች ለውጥ ለማምጣት መሰራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በተለያየ አካባቢ የሚታየውን የጤና ተግባራት አፈጻጸም ልዩነቶችን የተቀራረበ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ በቅንጅትና በኃላፊነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመሆኑም የጤና መረጃ ስርዓትን ማዘመንና ቀልጣፋ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ የመረጃን ዲጂታላይዘሽን ወሳኝ በመሆኑ የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስብዋል ።
በቢሮው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨምሳ በዘመቻው በሽፋንም ሆነ በጥራት ግቡ እንዲሳካ የባለድርሻ አካላት ሚናው የጎላ መሆኑን በማንሳት ምስጋና አቀርበዋል።
የተመዘገበው ስኬት በየደረጃው የሚገኙ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፉ በተሰራው ስራ የተገኘ በመሆኑን ይህን በሁሉም ተግባራት ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለጤና አገልግሎት የተሳካ በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል በመረጃና ሪፖርት ጥራት ላይ በመስራት ለላቀ ውጤት መትጋት እንደሚገባአቶ ወሰን አሳስበዋል።
በዘመቻው የተገኘውን ጠንካራ ጎን ቀጣይነት እንዲኖርና ጉድለቶችን በማረም ውጤትን ለማላቅ የድጋፍ፣ ክትትልና ቅንጅት እንዲሁም ግብዓትን የማሟላት ስራዎች መጠናከር እንደሚገባ በውይይቱ ላይ አጽንኦት ተሰጥተዋል ።
በጌታሁን ግርማ
