በክልሉ በገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ከታቀፉት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል 15206 የሚሆኑት ከተረጂነት ተላቀው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲችሉ ተደርጓል፦ዶ/ር ለማ መሠለ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም 5 “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል መርህ የሚሸጋገሩ ተረጂዎች ክልላዊ የምረቃ መርሃግብር በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ ደነባ ቦላ ቀበሌ ተካሂዷል።

በክልሉ በልማታዊ ሴፍትኔት ከታቀፉ 23669 የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ 15206 (64.3%) የሚሆኑት ከተረጂነት ተላቀው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከመቻል ባለፈ ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መደረጉን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ለማ መሠለ ገልጸዋል ።

የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ዘለቄታዊ ድጋፎች ተደርጎ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የመንግስትና የፓርቲ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም አንስተዋል።

የክልሉ መንግስት ባለፉት ጊዜያት የተረጂነት አስተሳሰብን ለመቅረፍ በክልሉ ለሚገኙ 4145 አባዎራዎችና እማዎራዎች የማይመለስ 131,285,935 ብር፣ 63 የውሃ ፓንፖችን፣ 20 የውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ መቻሉም ተጠቅሷል።

በምረቃው የተገኙ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው መንግስት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማደግ በሚያደርገው ጥረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መሬትን በማረስና በአከባቢ ያሉ ፀጋዎችን በአገባቡ በመጠቀም ራስን ከመቻል ባለፈ ለአገር ብልፅግና የሚበቃ ምርት ለማምረት እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ተወካይ አቶ መብራቱ መርክነህ እንደ ብልፅግና ፓርቲ ተረጂነትን በማስቀረት የበለፀገ ዜጋ ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሎማ ቦሳ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና፣ አከባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ

ባህሩ በላቸው በወረዳው 840 አባዎራዎችና አማዎራዎች ከተረጂነት ተላቀው እንደተመረቁ ተናግረዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል አቶ እሸቱ አየለ፣ አቶ አማኑኤል ዳንኤልና ወ/ሮ ወ/ሮ አበበች አሩሴ በበኩላቸው መንግስት ከተረጂነት እንዲላቀቁ ስላደረጉት ድጋፍ አመስግነው ከዚህ በሗላ በራስ ጥረት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ለመብቃት እንደሚተጉ ተናግረዋል ሲል ደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *