በዞኑ ያለውን ፀጋ በአግባቡ በመጠቀም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚገባ ተገለፀ

Spread the love

የፌደራል እና የክልል ተመራጮች ለዞኑ አስፈፃሚ አካላትና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታና የህዝብ ውይይት ግብረ መልስ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ሰጥተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አዝመራ አንደሞ እንደገለፁት ሁሉ አቀፍ በፌደራልና በክልል መንግስት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች የመንገድ፣ የውሃ እና የመብራት ስራ አፈጻጸም ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልፀው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

ህዝቡ ልማትን መጠየቅ ብቻም ሳይሆን ለልማት እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልፀው የዞኑን ህዝብ ሠላምና አንድነት አስጠብቆ መሄድ እንደሚገባ አክለው ገልፀዋል።

በዚህም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመንግስት ብቻ የሚመለስ ባለመሆኑ በሁሉም የልማት መስክ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማጎልበት ይገባል ብለዋል።

በዞኑ ያለውን ፀጋ በአግባቡ በመጠቀም የህዝቡን የልማት ጥያቄዎችን መመለስ ይገባል ያሉት አቶ አዝመራ በቡና፣በስንዴ፣ በፍራፍሬ እና አትክልት እንዲሁም በእንሰት ልማት የተጀመረው ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ሠላም ከሌለ የትኛውንም የልማት ተግባራትን ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ የሠላም እሴት ግንባታ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህር ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የክልሉ ምክር ቤት አባል አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በየደረጃው ተቀናጅቶ መስረት ይገባል ብለዋል።

ህዝቡ ለልማት ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው ያሉት አቶ አልማው የብልፅግና አንዱ መንገድ የህዝብን አቅም በማስተባበር ለልማት ማዋል በመሆኑ በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰሩ ያሉ የመንገድ፣ የድልድይ፣ ሆስፒታልና ሌሎችን በአግባቡ መምራት ይገባል ሲሉም ገልፀዋል።

በሠላምና ፀጥታ ከዞን ማዕከል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ የፀጥታ መዋቅሩ እና ባለድርሻ አካላት ህግ ከማስከበር አንፃር በትኩረት መሠራት እንዳለበትና የውይይት መድረኮችን እየፈጠሩ መሄድ እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።

በተለይ የተጀመሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች አልቀው ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈፃሚ አካላት ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ መሄድ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አንስተዋል።

እንደ ሀገር በተጀመሩ እንሼቲቮች ላይ በተለይ በግብርና ዘርፍ በስንዴ ፣በቅመማ ቅመም የተጀመሩ እንሼቲቮችን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የቴፒ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ወንድሙ ግርማ በበኩላቸው በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣በሠላምና ፀጥታ እንዲሁም በሌሎች ዙሪያ የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ይሠራል ሲሉ ገልፀዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትም በቀጣይ መሰራት አለበት ያሏቸውን አስተያየት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ማህበረሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በተቋማት የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በተለይ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፣በመናኃሪያ እና በጤና ተቋማት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ማሻሻል እንደሚገባ አንስተዋል።

በህብረተሰብ ተሳትፎ የተጀመሩ የመንገድ መሠረተ ልማት ስራዎችን ማስፋት እና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት መጨረስ እንደሚገባ ጠቁመው በሠላምና ፀጥታ ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎቸ ማህበረሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎችን ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በነዳጅ አቅርቦት በተለይ የቤንዚን እጥረትና የዋጋ ንረት ህዝቡን ለከፋ ችግር እየዳረገ በመሆኑ በሚገባ በመፈተሽ መፍታት እንደሚገባ በአፅንኦት አንስተዋል።

ያለንን ፀጋ በአግባቡ በመጠቀም ወደ ልማት መቀየር እና የተጀመሩ ኢንሼቲቮች የግብርና እና ሌሎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረው ሠላም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ አንዳንድ አካባቢ የሚስተዋሉ ጥቃቅን ችግሮች ሳይሰፉ መዋቅራዊ ውይይት በማድረግ መፍታት ይገባል ማለታቸዉን ሸካ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *