
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የወጪ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታና ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑን የሞሃን ኩባንያ ሊቀ-መንበር እና የህንድ ቢዝነስ ፎረም ሊቀመንበር ማዩር ኮታሪ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ በተለያዩ የማምረቻ ዘርፎች ላይ የተሰማራው የሞሃን ኩባንያ ሊቀ-መንበር እና የህንድ ቢዝነስ ፎረም ሊቀመንበር ማዩር ኮታሪ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራውን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በፖሊሲ ተግበራው በመንግስት የተወሰደው እርምጃ ብዙዎች ሲጠብቁት የነበረ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ተጠቃሚነት እንዲሁም ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገሪቱን ምጣኔ ኃብት በአግባቡ ለማስተዳደር፣ የወጪ ንግድን ለማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ለንግዱና አምራች ዘርፉ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን መደረጉ በጥቁር ገበያውና በባንክ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያጠብ ይሆናል ብለዋል።
አምራች ኢንዱስትሪው በውጭ ምንዛሬ በኩል የነበረበትን ክፍተት በመሙላት ምርታማነትን ለማሳደግና ተወዳዳሪነትን ለመጨመር የሚረዳ መሆኑንም ገልጸዋል።
ድርጅታቸው አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ለመተግበር የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን አስታውሰው፤ ፖሊሲው ይህን ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የፖሊሲው መተግበር በወጪ ንግድና ኢንቨስትመንት ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት ተወዳዳሪና ስኬታማ የሚያደርግ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በተመሳሳይ የወጪ ንግድ ገቢን በማሳደግ፣ አርሶ አደሩ ትክክለኛውን ገቢ እንዲያገኝና ፍትሃዊ ምጣኔ ኃብትን እውን ለማድረግም ይረዳል ብለዋል።
አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በመጨመር፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣት ለፈጣን ምጣኔ ኃብት እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ፖሊሲው ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የገበያ አቅም ለመጠቀም ቁልፍ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ መሆኑንም አብራርተዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የተቀመጠለትን ዓላማ እንዲያሳካ በተሰማሩበት የሥራ መስክ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑም አረጋግጠዋል።
በሚቀጥሉት አራት ዓመታት በማክሮ ኢኮኖሚ የማሻሻያ እርምጃዎች ምክንያት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ በ8 በመቶ ያህል እንደሚያድግ ይጠበቃል።
የዋጋ ንረት ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንደሚል፤ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻም 11 በመቶ እንደሚደርስም ይጠበቃል።
የመንግሥት ዕዳ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ እንደሚል፤ የወጪና ገቢ ንግድ ዋጋ ወደ 20 ቢሊየን ዶላር እንደሚያድግ፤ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ 8 ቢሊየን ዶላር ከፍ እንደሚልና ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ክምችትም ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ ይሆናል ተብሎ ይገመታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
