የመደመር እሳቤ የበይነ መንግሥታትን ግንኙነት በማጠናከር ችግሮችን በቅንጅት መፍታት የሚያስችል ዕድል መፍጠሩን የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ፡፡

Spread the love

በኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ የፌደራሊዝም ስርዓት ሥራ ላይ ከዋለ ከ30 ዓመት ቢያስቆጥርም አተገባበሩ ለነጠላ ትርክት ዳርጎ ቆይቷል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ግን በፌደራሊዝም ሥርዓት አተገባበር ላይ ያለውን ክፍተት ለመፍታት ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት መፈጠር እንዳለበት ታምኖበት ህጎች ወጥተዋል፡፡

በዚህም የክልል መንግሥታት የእርስ በርስ እና ከፌደራል መግሥቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚወስን የበይነ መንግሥታት አዋጅ ገቢራዊ ተደርጓል፡፡

የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ከለውጡ በኋላ የመደመር እሳቤ የበይነ መንግሥታትን ግንኙነት በማጠናከር ችግሮችን በቅንጅት መፍታት የሚቻልበትን እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

የለውጡ መንግሥት የክልል መንግሥታት ችግሮቻቸውን በጋራ መፍታት የሚችሉበት አሰራር ከመፍጠርም ባለፈ በወንድማማችና እህትማማችነት ላይ የተመሰረተ መተማመን እንዲኖር አድርጓል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ክልሎች በመካከላቸው የሚፈጠረውን ችግር በውይይትና በንግግር መፍታት የሚችሉበት የፖለቲካ ዐውድ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባበር በክልሎች መካከል ያለው ቅንጅት ህጋዊ መልክ የሚይዝበት አሰራር ገቢራዊ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለመገንባት የጋራ ትብብር ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ችግሮችን መከላከል ሳይሆን በህዝቦች መካከል ያለውን ሁለንተናዊ መስተጋብር ማጠናከር ዋስትናችን ሊሆን ይገባል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *