




የቤንች ብሔር ዘመን መለወጫ “ቢስት ባር” በዣዥ ቀበሌ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ ባስተላለፉት መልዕክት የቢስት ባር በትክክለኛው ወቅት የተከበረ ህዝቡ ሀብት ንብረት ማፍራት በቻለበት ወቅት መከበሩን ተናግረዋል ።
የቢስት ባር ለይቅርታና ለምስጋና የሚከበር የአዲስ ብስራት ማብሰሪያ የአዲስ ዓመት መለወጫ ነውም ብለዋል።
ይህንን ታሪካዊ ስፍራ የጠበቁትን ዣዥቴትን አመሰግናለሁ ያሉት አቶ ጸጋዬ ወጣቱ ትውልድ ለዓለም ቱሪዝም መሳቢያ ስፍራ ሆኖ እንዲለማ በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል ።
የቤንችቴት፣የሼቴትና ሜርቴት የቤንች ህዝብ የማንነት ምሳሌዎች በመሆናችሁ እናከብራችኋለን ሲሉም በመልዕክታቸው ገልጸዋል።
በዚሁ ክብረ በዓል ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን ቢስት ባር በዓሉ በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ እሸት የሚቀመስበት ፣ የጥጋብና የአዲስ ብስራት ጅማሬ ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ለዚህም ህዝቡ ፈጣሪያቸውን በአደባባይ በጋራ የሚያከብሩበት ትልቅ በዓል ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
ቢስት ባር ሰላም ነው ። ቢስት ባር ልማት ነው። ቢስት ባር አንድነታችን ፣ ፍቅርና መተሳሰባችን በጋራና በተግባር የሚገለጽበት የአደባባይ በዓላችን ነው።
ቢስት ባር የከፋፋይና ነጣጣይ ትርክቶችን አፍርሰን አንድ በሚያደርገን ገዥ ትርክት ላይ በመቆም መጻኢ ዕድልና ተስፋችን እንዲሁም ብልጽግናችንን የምናረጋግጥበትና በጋራ ቃል የምንገባበት ቱባ ባህላችን ነው ብለዋል።
አንድነታችንና ህብረታችን ከአለት እንደሚጠነክር የተገነዘቡ አካላት የቤንች ህዝብን በወንዝ ፣ በተራራ ፣ በመልክዓ ምድር ፣ አንተ ከዚያ ነህ ፣ አንተ ደግሞ ከዚህ ነው እያሉ የመለያየትና የመነጣጠል ትርክታቸውን ሲዘሩ ይታያሉም ብለዋል።
ይህ ሁሉ ልፋታቸውና ከንቱ ጥረታቸው ፍሬ የሌለውና ያለፈበት አጀንዳ መሆኑን ለመረዳት ዛሬ ከተገኘንባት ከዣዥ በላይ አስረጂ ሊቀርብ አይችልም ብለዋል።
ለዛሬ ማንነታችን መሰረትና መነሻ ቦታ ላይ በጋራ ቆመን ማክበራችን ነገ ከዚህ በተሻለ አንድነት ፣ ጥንካሬና ወንድማማችነትን ይዘን ወደ ምንመኘው ብልጽግና ለማምራት ትክክለኛ መስመር ላይ መሆናችንን ማሳያ ነው ብዬ አምናለሁ ሲሉም አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል ።
የ2017 የቤንች ብሔር ዘመን መለወጫ “ቢስት ባር ” በቤንች ነገስታቶች የምርቃት ስነስርዓት በበዓሉ ላይ አድርገዋል።
በዣዥ ቀበሌ የነበረው የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫ “ቢስት ባር”በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ተከብሮ ውሏል።
