






የክልሉ ደን፤ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ከFOLUR ፕሮጀክት ከክልሉ ቡና ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን ጋር በመተባበር የቡና ምርታማነት ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አማካሪ እና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ መላኩ፤ በክልሉ ቡና እና የቅመማቅመም ምርቶች የማኅበረሰቡን ኑሮ ከመቀየር ባሻገር ለኢኮኖሚ ዕድገት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል።
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እንደሀገር ቡናን አምርተዉ ለማዕከላዊ ገበያ ከሚያቀርቡ ክልሎች መካከል ተጠቃሽ እንደሆነም ያብራሩት አቶ ዮሐንስ መላኩ፤ የተለያዩ የቡና ምርታማነት ማሳደጊያ ፓኬጆችን በመተግበር ቡናን በጥራትና በብዛት በማምረት ክልላዊ አቅርቦትን ማሳደግ ይገባልም ብለዋል።
ቡና በክልሉ የቱሪዝም ማዕከል እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራም ያስታወቁት ኃላፊዉ፤ የቡና ምርታማነቱ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ እንዲል ምርት የቀነሱ እና ያረጁ የቡና ማሳዎችን ማደስ እንዲሁም አዳዲሶቹን በስፋት ከመትከል ባሻገር ምርታማነቱ እንዲሻሻል ከተለያዩ ምርምር ተቋማትና አካላት ጋር በተቀናጀ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
ቡናን ከተለምዷዊ የአመራረት ዘይቤ በማላቀቅ በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የቡናውን ዘርፍ በማዘመን ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ይሰራልም ብለዋል አቶ ዮሐንስ መላኩ።
የቡና ምርታማነት እንዲጨመርና የጥራት ደረጃው ከፍ በማድረግ እንዲሁም አቅርቦቱን በማሳደግ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንደክልል ትኩረት ተሰጥተው ሥራዎች እንደሚከናወኑም የገለጹት የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ ናቸው።
ለቡና ምርታማነት መጨመር አጋዥ የሆኑ ሙሉ ፓኬጆችን አሟጦ መጠቀም አማራጭ የለለው ጉዳይ ነው ያሉት አቶ አሥራት መኩሪያ፤ እስከታችኛው መዋቅር ሥራዎችን በንቅናቄ መምራት እንዲሁም ቡና ላይ ጥናትና ምርምር በሚያካሂዱ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለአርሶ አደሮች ልምድ ልውጥ ማድረግና የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ይሰራልም ብለዋል።
ክልሉ ካለው አቅም አንጻር ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ በስፋት ማቅረብ እንዲያስችል በቡና ልማት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን መከታተልና ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ እንዲሀም አርሶ አደሮችን መደገፍና በቡና ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶችን የማበረታታቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተጠይቋል።
በፍቅር ከበደ
