




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት የ2018 ዓ/ም የመሠረተ ልማት ክላስተር ተቋማት የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም እና የቀጣይ አቅጣጫዎች የተግባቦት መድረክ በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል ።
በዚህም የክላስተር ተቋሟት የሆኑት የክልሉ ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ፣ የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ እና አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮዎች የ1ኛ ሩብ ዓመት ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።
በመሆኑም በሩብ ዓመቱ የአራቱ ተቋማት ሪፖርት ላይ ያለው አፈጻጸም አበረታችና ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል።
በተቋማት የሚታየው የቅንጅታዊ አሠራር አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ያሉት አስተያየት ሰጪዎች ከከተማ ኮሪደር ጋር ተያይዞ የመብራትና የቴሌኮሙኒኬሽን ተደራሽነትን መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል ።
አያይዘውም በፕሮግራም የሚመሩ በጀቶችን ከብክነት በጸዳ መልኩ መምራት ተገቢ ነቱ ተገልጿል። በማዕድን ዘርፍ በ1ኛ ሩብ ዓመት ከ207 ኪግ ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ መግባቱን እያደገ ያለ አፈጻጸም ስለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተነስቷል።
ዜጎችን በማህበር አደራጅቶ የመኖሪያ ቤት ቦታ ከማስተላለፍ ረገድ ሁሉም መዋቅሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የዜጎችን ቅሬታ መቀነስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
መሠረተ ልማትን ተደራሽ ከማድረግ ረገድ የሕብረተሰብ ተሳትፎን የዕቅድ አካል አድርጎ አጠናክሮ መሥራት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ መንገድና ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ህዝብ ጋር ቀረብ ብሎ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል ።
ሕዝብ ቅሬታ የሚያነሳባቸው እንደ ትራንስፖርት ዘርፍ ፣ ማዘገጃ ቤታዊ አገልግሎት ፣ የከተማ ውሃ አገልግሎት እንዲሁም የመብራትና የስልክ መሠረተ ልማቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ ውስጥ እየተገነቡ የሚገኙትን ሶስቱን መናኸሪያዎች ድጋፍ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ክፍት እንዲሆኑ ጥረት ይደረጋል ብለዋል ኃላፊው።
ሁሉም ተቋማትን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ተግባራትን በቅንጅት በማከናወን ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል ።
አቶ ፋጂዮ አክለውም የሕብረተሰብ ተሳትፎን ሁሉም የክላስተሩ ተቋሟት ባህል አድርጎ በመስራት ውጤት ማስመዝገብ ይገባቸዋል ያሉ ሲሆን በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ላይ እየታየ ያለዉን ውጤት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።
