
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የዘንድሮ ማርች 8 ( አለምአቀፍ የሴቶች ቀን) በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ እንደገለጹት፥ በሁሉም የክልሉ መዋቅሮች ቀድሞ በወረዳ መነሻ ዕቅድ መሠረት ቀኑ በተለያዩ ኩነቶች እና በመስክ ጉብኝት ይከበራል ብለዋል።
በዓሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ነው ወ/ሮ ገነት የገለጹት።
የበዓሉ ዓላማ ሞዴል የሴቶች የልማት ህብረቶችን እንዲጠናክሩ በማድረግ የሴቶች የቁጠባ ባህል ለማዳበር በንቅናቄ ሴቶች እንዲቆጥቡ ማድረግ፣ በግብርናም በኢንደስትሪ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት እና የሚሸጡበት ኢግዚቢሽን እና ባዛር ማካሄድ እንዲሁም የማህፀን በር እና የጡት ጫፍ ካንሰርን ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ የአንድ ሳምንት ንቅናቄ ለማድረግ እና የህዳሴ ግድብ ተሳትፎ ግንባታው እንስኪጠናቀቅ ድረስ ቦንድ የመግዘት ስራዎችን አጠናክረው ለማስቀጠል መሆኑን ኃላፊዋ ጠቁመዋል።
በዓሉን በማስመልከት በኮንታ ዞን፣ አመያ ከተማ አስተዳደር በሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀት የተሰሩ ስራዎችን የሚያሳይ በኤግዚብሽን እና ባዛር እንደሚካሄድ የገለጹት ወ/ሮ ገነት የፌደራልና የከልል ሴት አመራሮች በጋራ በመሆን በዞኑ በሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀት የተሰሩ ስራዎችን ተዘዋውረው እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።
በዓሉ በይፋ በኮንታ ዞን፣ አመያ ከተማ የፌዴራል እና የክልል አመራሮች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅት በድምቀት መከበር ይጀምራል ኃላፊዋ እንዳስታወቁት።
በዕድገቱ በዛብህ
