




ሸካ ዞን የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰባተኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫን አስመልክቶ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በጌጫ ከተማ ምክክር አካሂዷል ።
የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና የላቀ መሆኑም በመድረኩ ተጠቅሷል ።
የምርጫው አተገባበርና የህግ የበላይነትን በማክበር በፖሊቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደርግ ፉክክር ሚዛኑን መጠበቅ እንዳለበትም የተገለጸ ስሆን ለህግ ተገዢ መሆን በሀገር ግንባታና በዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት ውስጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው ተብሏል ።
የተፎካካሪ ፖሊቲካ ፓርቲ ተወካዮች ለሰላምና ለዴሞክራሲ መጎልበት የድርሻቸውን ከመወጣት ባሻገር ደጋፊዎች እና አባሎቻቸው የተጀመረውን የምክክር ባህል አጠናክሮ እንዲያስቀጥሉ መስራት እንደሚገባም ተጠቁሟል ።
በተለይም በሸካ ዞን በተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች የተሻለ እንደሆኑ የጠቀሱት የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ መፍታት አስፈላጊ ስለመሆኑም አብራርተዋል ።
በሸካ ዞን የፖሊቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ፓርቲ ተወካይ አቶ አስማማው ዓለሙ በመድረኩ እንደተናገሩት በፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች በምርጫ ወቅት የሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት አጋዥ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
በአገራችን ኢትዮጵያ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚደረገውን ጥረት በመተጋገዝ ማሳካት ይገባል ያሉት አቶ አስማማው የምክክር ባህሎችን በማዳበር የፖሊቲካ ፓርቲዎች በትብብር እንዲሰሩም ጠይቀዋል ።
በየመዋቅሩ የሚገኙ የፖሊቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመነጋገር እንዲፈቱም አቶ አስማማው አሳስበዋል ።
በዞኑ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤቱ ምክትል ሰብሳቢውና የብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ አለማየሁ ዓለሙ በበኩላቸው የተጀመሩ የንግግርና የምክክር ባህል እንዲዳብር በጋራ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በምርጫ ቦርዱ የተደነገጉ ህጎችን በማክበር መፎካከርና የህግ የበላይነትን በማክበር በሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ጉድለቶችን በትብብር እያረሙ እንዲቀጥሉም አንስተዋል ።
በሀሳብ መወዳደርና መፎካከር በትብብር ውስጥ መሆን ይገባል ያሉት አቶ አለማየሁ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የምናሳየው መልካም ስራዎች ቀጥሎ ለምናካሂደው ምርጫ ተስፋ መሆን አለበት ነው ያሉት ሲል የሸካ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
