




“ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፓናል ዉይይት በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ጌታቸው ኬኒ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ በሀገራችን ታሪክ የሁሉንም የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ቃል ኪዳን ሰነድ የፀደቀበት ቀን ስለሆነ በዓሉን ስናከብር ብዝኃነትን ማዕከል በማድረግ የጋራ አንድነታችንን በማጠናከር መሆን አለበት ብለዋል።
የዘንድሮውን በዓል ልዩ የሚያደርገው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጠናቀቀበት፣የባህር በር ለማግኘት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥያቄ የተጀመረበት ፣ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ከፊሉ በተጠናቀቁበት እና ከፊሉ በተጀመሩበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራችን ከውስጥና ከውጭ የሚገጥሟትን ፈተናዎችን በማለፍ የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተጋች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።
ህዝቡ አብሮነት፣መቻቻል እና የመተሳሰብ ባህልን በማጎልበት ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለሀገራችን ልማት እና መልካም አስተዳደር ተስፋዎች ከመንግሥት ጎን እንድሰለፍም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው በዓሉ የእርስ በርስ ትስስር በማጠናከር ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበት እና ለሁለንተናዊ የልማት ዕድገት ተሳትፎ መረጋገገጥ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ተናግረዋል።
እርስ በርስ መቀራረብ ያሉንን እምቅ ሀብቶቻችን እና ቱባ ባህላችንን ለማስተዋወቅ፣ለማሳደግ እና እኩል ተጠቃሚ ለመሆን የሚረዳ መሆኑን ገልፀው ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከርና በሀሳብ የበላይነት በመተማመን፤ የፌደራሊዝም ሥርዓትን ለማሳለጥ ሁሉም የድርሻቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
በካሳሁን አሰፋ
