




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ስሰጥ የነበረው 2ኛ ዙር ሀገር ዓቀፍ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
“በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እምርታ” በሚል መርህ ቃል ላለፋት ዘጠኝ ተከታታይ ቀናት በቦንጋ ከተማ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና የአመራሩን እውቀት፣ ክህሎትና የመፈጸም አቅም በሚገነቡ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ያተኮረ እንደነበረ ተገልጿል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ተገኝተው በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥ በማኅበረሰቡ ዘንድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ አመራሩ የአስተሳሰብና የባህር ለውጥ ማምጣት አለበት ብለዋል።
በምንከተለው የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ሂደት በሁሉም ዘርፎች ቀጣይነት ያለው በእጅጉ እያደገ የሚሄድና በማህበረሰብ ለውጥና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ዕድገት በማስመዘገብ ሁለንተናዊ ብልፅግና ልናረጋግጥ ይገባል ስሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።
አመራሩ በትናንሽ ድሎች ሳይዘናጋ በትልቁ አቅዶ አልቆ መፈጸም አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ከራስ የሚጀምር የሥራ ባህል ማሻሻል ይጠበቃል ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኘው አመራር ከጠባቂነት በመላቀቅ፣ ማኅበረሰብን በማስተባበር እንዲሁም በራስ አቅም ፈጠራና ፍጥነት በማከል በውጤት የታጀበ ተግባር መፈጸም እንደሚጠበቅበትም ነው ያስገነዘቡት።
ህዝብን ለማገልገል በተሰጠው አጭር ጊዜ አሻራ ጥሎ ማለፍ ከእያንዳንዱ አመራር እንደሚጠበቅ ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ውጤት አልቦ በኾኑ ተግባራት ጊዜ ማጥፋት እንደማይገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።
መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋትና በሁሉም ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ ማሳደግ እንደሚገባ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የተጀማመሩ የኢንሼቲቭ ተግባራትን ቀጣይነት ባለው መልኩ አጠናክረው ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የግብርና ሽግግር በማሳለጥ የገጠር ሽግግርን በተጨባጭ ማረጋገጥ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ግብርናን በማዘመን ለጠቅላላው ሃገራዊ ምርት የሚያበረክተውን ድርሻ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
አመራሩ ተግባራት የመፈጸም አቅም በማጎልበት ከወቅቱ ጋር አብሮ መጓዝ እንዳለበት በማመልከት እያንዳንዱን ተግባራት በፈጠራ፣ ፈጥነትና በዝላይ መፈጸም እንዳለበትም ተናግረዋል።
በመደመር መንግሥት መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣትና የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የተጀመረው ጉዞ እንዲሳካ የአመራር ሚና ወሳኝ መኾኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አመራሩ ለወቅታዊ ችግሮች ሳይበገር የመፍትሔው ምንጭ መኾን አለበት ብለዋል።
አመራሩ በወሰደው ስልጠና የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በማከል በቀጣይ የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረትና ትጋት መስራት እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
