
ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የቴክኒክና ሙያ የአሰልጣኝ መምህራን አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት መደረጉን የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ሚኒስቴሩ ከነገ ጀምሮ “ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት” በሚል መሪ ኃሳብ ለ12 ቀናት የሚቆይ ሥልጠና እንደሚያስጀምር አስታውቋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ ሥልጠናው አዲስ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ወደ ሥራ መግባቱን መሠረት ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው በዚሁ ሥልጠና 24 ሺህ የሚደርሱ ሰልጣኞች እንደሚሳተፉና ከነሐሴ 22 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 በ17 ማዕከላት በሁሉም ክልሎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ሥልጠናው አዳዲስ የሪፎርም እሳቤዎችንና የፖሊሲ ጉዳዮችን አረዳድ ተቀራራቢ ወደ ሆነ ግንዛቤ በማድረስ የዘርፉን እሳቤዎች በውጤታማነት ለመተግበር እንዲያስችል ታሳቢ ያደረገ ሥልጠና መሆኑን አስረድተዋል።
ሥልጠናው ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል የሰው ኃይል ለማፍራት ያለመ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሥልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ አሰልጣኞች ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
ሥልጠናው አዳጊ፣ ቴክኒካዊና ባህሪያዊ ብቃትን በማላበስ የአሰልጣኞች አቅም የሚገነባበት መሆኑን ተናግረዋል።
በነገው ዕለት የሚጀመረውን ሥልጠና በውጤታማነት ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ ሁሉም አካል የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
