




የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አገር አቀፍ የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽንን ምክንያት በማድረግ “አረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን በማደረግ ሂደት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሚና “በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
ከውይይቱ ጎን ለጎንም በኃይል ቁጠባ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡና፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሽያጭ የፈጸሙ ኩባንያዎችና ድርጅቶች እውቅና ተሰጥቷል።
በሥነ-ስርዓቱ ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶክተር)፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ ሚኒስትር ደኤታዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በውይይቱም በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ያለበት ደረጃ፣ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችና የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሀሳቦች ተዳሰዋል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ ባለሥልጣኑ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በስፋት ሥራ ላይ እንዲውል ጥናት ላይ የተመሰረቱ ሥራዎችን ማካሄድ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
መሰረተ ልማት ግንባታ በሰፊው ማካሄድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን ለማስፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም እንደ አገር የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ በመቅሰም ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
ባለሥልጣኑም ዘርፉን ዝቅተኛ ታሪፍ የሚኖርበትን አሰራር ለመዘርጋት የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት እየተሰራ ነው።
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ይዘንጋው ይታይህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መጠቀም ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን፣ ለመቀነስ በመተንፈሻ አካላት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን የበለጠ ሥራ ላይ ለማዋል መንግሥት የፖሊሲና ስትራቴጂዎች ዝግጅት እንዲሁም መመሪያዎችን በተመለከተ ዘርፉን ለማጠናከር የሚረዱ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግሥት የግል ባለሃብቱን ለማበረታታት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ያሉት አቶ ይዘንጋው ፤ ሙሉ በሙሉ ተፈታትተው የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መፈቀዱን ጠቅሰዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ማድረጊያ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መፈቀዱን የገለጹት አቶ ይዘንጋው ባለሃብቱን ለመሳብ በመሬት አቅርቦትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
እንደ ከፍተኛ ባለሙያው ገለጻ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ቻርጅ ማድረጊያ መሳሪያዎች ወደ አገር እንዳይገቡ ለማድረግ የሚያስችል ስታንዳርድ እየተዘጋጀ መሆኑንም አመልክተዋል።
የዲቨንተስ ቴክኖሎጂ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የውይይቱ ተሳታፊ ዳንኤል ግዛው በበኩላቸው በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መስክ የግሉን ዘርፍ ይበልጥ ለማሳተፍ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የሃይል አቅርቦትና ስርጭት ከተስተካከለ፣ በዘርፉ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች በመደገፍ ወደ ኢንዱስትሪው እንዲቀላቀሉ ከተደረገ ውጤት ማምጣት ይቻላል ሲሉም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የኢንቫይሮመንታል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ምንተስኖት ግዛው(ዶክተር) እንዳሉት፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ መስራት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር አገሪቱን ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ መቀነስ ያስችላታል።
በመሆኑም አገሪቷ ያላትን የጸሃይና ነዳጅ ሀብቶችን በመጠቀም በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሃይል አቅርቦትን ለማሻሻል መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር(ግሪድ) የራቁ ቦታዎች ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እንዲስፋፋ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎችም ትኩረት ይፈልጋሉ ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
