የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የአመራር ቁርጠኝነት መታከል እንዳለበት ተጠየቀ።

Spread the love

በአቶ ፍቅሬ አማን፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የሱሪ ወረዳ አጠቃላይ አመራሮች ጋር በኪቢሽ ከተማ ውይይት አድርገዋል።

የክልሉ መንግሥት በቀጠናው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሰራ መኾኑን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፥ ይሁን እንጅ የሚፈልገውን አውንታዊ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የአመራር ቁርጠኝነት መታከል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአርብቶአደር አከባቢ ነዋሪዎች ሠላማቸውን እየጠበቁ የተፈጥሮ ሀብታቸውን ተጠቅመው ህይወታቸውን በዘላቂነት እንዲያሻሽሉ አመራሩ የመሪነት ሚናውን በተገቢው መወጣት እንዳለበትም አቶ ፍቅሬ በአጽንኦት ተናግረዋል።

በቀጠናው ሠላም ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደኾነ ያመለከቱት አቶ ፍቅሬ፥ ከአጎራባች ህዝቦች ጋር የእርስበርስ ትስስር ማጠናከር እንዲሁም የአከባቢውን ሠላም በዘላቂነት መጠበቅና የህግ የበላይነትን በማስፈን የተጠያቂነት አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አመራሩ በግምባር ቀደምትነት ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመከላከል ለዘላቂ ሠላም መስፈን በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ያስገነዘቡት አቶ ፍቅሬ፥ ችግሮች ስከሰቱም የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ትኩረት የሚሻ ተግባር መኾኑን ጠቁመዋል።

በአከባቢው ለሚፈጠረው የፀጥታ ችግር ዋነኛ ምክንያት የባህል ተጽዕኖ መኾኑን የገለጹት የሱሪ ወረዳ አመራሮች፥ የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ የሚቀይሩ ስራዎች በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠይቀዋል።

በሁሉም ዘርፍ የድጋፍና ክትትል ሥራው መጠናከር እንዳለበት ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችም ደረጃ በደረጃ መፍታት እንዳለበት አንስተዋል።

ተቋማዊ አደረጃጀትና መዋቅራዊ ግኑኝነትን በማጠናከር የመንግሥት አግልግሎት በሁሉም ደረጃ ለአርብቶአደሩ ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ነው በመድረኩ የተገለጸው።

የአከባቢው ምሁራን የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እንዲሁም ውስብስብ የፀጥታ ችግሮችን በተቀናጀ መልኩ ለማስተዳደር በሚደረገው ያልተቋረጠ ጥረት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።

የክልሉ መንግሥት የአርብቶአደሩን አከባቢ የፀጥታ ችግሮች በመቅረፍ ልማት ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በቀጠናው አውንታዊ ውጤት እያስገኘ በመኾኑን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ተሳታፊዎቹ የገለፁት።

ተሳታፊዎቹ የአከባቢውን ሠላም በማጽናት ወደ ልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በተሟላ መልኩ ለመሻገር ቁርጠኛ መኾናቸውን በመግለጽ፥ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ መድረኩ በስኬት ተጠናቋል።

በውይይት መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ የአመራሮች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የምዕራብ ኦሞ ዞን እና የሱሪ የወረዳ የአመራር አካላት ተሳትፈዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *