




በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ የለውጡን ጉዞ የሚደግፍ ደማቅ ሕዝባዊ ሠልፍ ተካሂዷል።
በሰልፉ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት በክልሉ የተመዘገቡ መሠረታዊ የፖለቲካና የልማት ድሎችን አጉልተዋል።
አቶ የሺዋስ በንግግራቸው ወቅት እንደገለጹት ከለውጡ በፊት የነበረው ሥርዓት ዜጎችን በገዛ ሀገራቸው ባዳ ያደረገ፣ ድምፅ የታፈነበትና የሕዝብ ጥያቄ የማይሰማበት “የጨለማ ዘመን” ነበር ብለዋል።
ሆኖም በመጋቢት 24 የመጣው ለውጥ ይህንን ታሪክ በመቀየር፣ በተለይም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ለዘመናት ስያነሱት የነበረው የክልልነት ጥያቄ በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረጉን በለውጡ የተገኘ ታላቅ የፖለቲካ ድል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተጨባጭ የልማት ስኬቶችና የማኅበራዊ አገልግሎቶች
ባለፉት ዓመታት በክልሉ መሠረታዊ ለውጥ ያመጡ ፕሮጀክቶች መከናወናቸውን ነው የገለጹት አቶ የሺዋስ።
ለአብነት በመሠረተ ልማት የቱሪዝም መዳረሻ ሎጆች ግንባታ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ መስፋፋት፣ እንዲሁም የመብራትና የመንገድ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች የለውጡ ተጨባጭ ፍሬዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በማኅበራዊ አገልግሎት የጤና ተቋማትና የሆስፒታሎች መስፋፋት፣ እንዲሁም የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ማደግ የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻሉን ጠቁመዋል።
በግብርና አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የግብርና ልማት ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ የሺዋስ አያይዘውም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ የሀገርን አንድነት ከማስከበር ባለፈ፣ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ሀገሪቱን ከፍ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።
በመጨረሻም መጪው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሕዝቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የብልጽግና ፓርቲን መምረጥ የተጀመረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ማረጋገጥ መሆኑን በመግለጽ ነዋሪዎች ለፓርቲው ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
በዕለቱ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መጋቢት 24 ቀን የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ስብራቶች ለመጠገን መሰረት የጣለ ታሪካዊ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት በመደመር እሳቤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ጨምሮ በአረንጓዴ አሻራ፣ በኮሪደር ልማት እና በበጋ መስኖ ስንዴ አብዮት ውጤቶች መመዝገባቸውን ዋና አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል።
በተለይም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተከናወኑ የልማት ስራዎችን በማንሳት፦የሀላላ ኬላ፣ የዝሆን ዳና እና የደንቢ ፋፏቴ ሎጆች መገንባታቸው ክልሉን የቱሪስት መዳረሻ አድርጎታል።
በቴፒ፣ በሚዛን አማን እና በቦንጋ ከተሞች የቡና ቅምሻ፣ ላቦራቶሪ እና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል እንዲቋቋም ተደርጓል።
ይህም ክልሉ በሀገር ደረጃ ሁለተኛው ከፍተኛ የቡና አቅራቢ እንዲሆንና የቡና ጥራት እንዲሻሻል ረድቷል።
አቶ አበበ ማሞ አክለውም የለውጡ መንግስት የህዝቡን የክልል መደራጀት ጥያቄ በድፍረት መመለሱን እና በዞኑ የነበረው የፀጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ማድረጉን ገልጸዋል።
የተጀመረው የሰላም እና የልማት ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የቴፒ ከተማ ከንቲባ አቶ ገላቲያስ ሻሜ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት እንደሀገር በኢኮኖሚ፣በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስኮች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
ቴፒ ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድ ተምሳሌት መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህንኑ ፀጋ በመጠቀም ሰፊ የልማት እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም የመሰረተ ልማት ግንባታ በከተማዋ የኮሪደር ልማት እና ከ3 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በህዝብ ተሳትፎ ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።
ለዚህም የሚሆን ልማት ስራዎች የሚውል ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸው፣ ለዚህም የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና የዞኑ ህዝብ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል ሲል የሸካ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
