ክልላዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግሥት እና የብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ አመት የተግባር አፈጻጸም እየተገመገመ ይገኛል።

ክልላዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባም ነው በአፈጻጸም ግምገማ መድረኩ የተገኙት አመራሮች የገለጹት።

የወጣቶችና የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ማደግ አንዳለበት የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች፥ የተጀመረው የአባልና አመራር ማጥራት እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአደረጃጀት ውጤታማነትንም በየጊዜው በመገምገም ውጤት በሚያስገኙ ተግባራት ላይ ማተኮር አስፈላጊ እንደሆነም ተነስቷል።

በፓርቲ መሪነት እየተከናወኑ ባሉት መደበኛና ወቅታዊ የመንግሥት ተግባራት በተሻለ መልኩ ውጤት እየተመዘገበ መኾኑን በመግለጽ የተገኘውን ውጤት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በእናቶችና ህፃናት ጤና አጠባበቅ ላይ በክልሉ ያለው ደካማ የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽነት አሉታዊ ተዕጽኖ እያሳደረ በመኾኑ የክልሉ መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም ተነስቷል።

ከመደበኛ የጤና አግልግሎቶች አኳያ ከኅብረተሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደርና የአግልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት በፓርቲው መሪነት በተከናወነው ውይይት አውንታዊ ለውጥ መመዝገቡ በአስተያየት ተገልጿል።

በክልሉ የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት ለማጠናከር በተላይም በብሄረሰብ በዓላት የታየውን መልካም ዕሴት በማስቀጠል መዋቅራዊ ጥልቀት በመፈጠር ክልላዊ አንድነት ማጠናከር እንደሚገባም ነው አስተያየት ሰጪዎች ያነሱት።

በግብርና ዘርፍ በኢንሼቲቭ የተጀመሩ የግብርና ዘርፍ ተግባራት ውጤታማ መኾናቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ ይህን ተሞክሮውን በመቀመር ሌሎች ተግባራትንም በአደረጃጀት መምራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ የተጀመረው ተግባር አበረታች እንደኾነ የተገለጸ ሲሆን ሠላምን በማጽናት ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማረጋገጥ በየአካባቢ ያሉ የፀጥታ ስጋቶች መለየትና መገምገም አስፈላጊ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በከተሞች የኑሮ ውድነትን ለማቅለል የተጀመሩ ኢንሼቲቮች ማጠናከር እንደሚገባ ያሳሰቡት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ በክልሉ መንግሥት አቅም መፈታት ባለባቸው ጉዳዮች የህዝብ የልማት አቅሞችን በማቀናጀት መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል የተጀመረው ተግባር የሁሉም ባለድርሻ አካላት የርብርብ ማዕከል መኾን እንዳለበትም ተነስቷል።

የክልሉን ልማት ለማሳለጥ የገቢ አቅም መሻሻል የሚገባ በመኾኑ፥ የገቢ መሠረቶችን ማስፋት እንደሚገባና ለገቢ ጉዳይም በየደረጃው ያለው አመራር ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።

ነባር ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ለኅብረተሰቡ ተገቢውን አግልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል እንደሚገባ ያስገነቡት ተሳታፊዎቹ፥ በበጀት ዓመት በጉድለት የታዩ ጉዳዮችን በመለየት መፍታት ይገባል ብለዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *