የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በማዳመጥና ምላሽ በመሰጠት እየተሰሩ ያሉት ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል :- አቶ ፍቅሬ አማን

Spread the love

በከተሞች የህዝብ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለማዳመጥና ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችል የህዝብ ውይይት መድረክን አስመልክቶ ክልላዊ የዘርፍ አመራሮች ውይይት መድረክ የክልል የሚመለከታቸው ተቋማት አመራሮችና የከተማ አስተዳደር አመራሮች በተገኙበት በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ባለፉት ዓመታት ከከተማ ነዋሪዎች ጋር በተደረጉት ህዝባዊ የውይይት መድኮች የተነሱትን መሰረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳድር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ መፍታት መቻሉን ገልጸዋል።

በከተሞች የነዋሪውን መሰረታዊ ጥያቄ በማዳመጥና ከልብ ተረድቶ አጥጋቢ ምላሽ መስጠት እንዲሁም በፍጥነት የማይመለሱ ጊዜ የሚሹ ጉዳዮችን ከህዝብ ጋር ተነጋግሮ ተግባቦት መፍጠር የወቅቱ ትልቅ አጀንዳ በመሆኑ በልዩ ትኩረት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

በዚህም በከተሞች በየማህበራዊ መሠረቱ የተቀናጀና የተደረጃ የነዋሪውን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል ስራዎችን የሚያሳልጥ ተግባራት ማከናወን ዋናኛ ተግባር አድርጎ መምራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመደመር መንግስት እሳቤዎች መሪነት ባለፉት ዓመታት የተገኙ ድሎችን ተከታታይነት ባለው መንገድ በህዝብ ግንኙነት ስራዎች ማስተዋወቅና ለህዝብ ግልፅነት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አመራሩ ደክሞ በመስራት፣ ያሉትን መልካም ዕድሎችን ተጠቅሞ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን መመለስ፣ የኑሮ ውድነት ማቅለያ ተግባራትን ማጠናከር፣ የአምራች እና ሸማች ገበያ ትስስር ማስፋፋት፣ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ ፈጥኖ ማጠናቀቅ፣ የገጠር ሞዴል መንደር ምስረታ ስራዎችን በጥራትና በተቀመጠው ጊዜ ትኩረት ሰጥተው ማጠናቀቅ እንደሚገባም በአንክሮ አንስተዋል።

7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በከተምች ፍጹም ሰላማዊ፣ ነጻ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያለው፣ በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ባለው መንገድ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው ያለው አመራር በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ እንደገለፁት የከተሞችን ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በውል በመገንዘብ የህዝብ እርካታ ለማረጋገጥ መንግስት ያስቀመጣቸውን ግቦችን ለማሳካት በፍጹም ትጋት ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በመደመር መንግስት ዕይታ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በከተሞች ፈርጀ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ከፍተኛ ልማትና ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉንም አንስተው አሁንም ቢሆን ህዝብ የሚያነሳቸው ትክክለኛ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ኃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህንን ዕድገትና ስኬቶችን ለማደብዘዝና ለመቀልበስ የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ጽንፈኛ ኃይሎች አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን ለህዝብ ማጋለጥና የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችን ለህዝብ ማስገንዘብ ተገቢ መሆኑንም አንሰተዋል።

በመድረኩ የተገኙት የከተማ አስተዳደሮችና የክልል ተቋማት አመራሮች በየአካባቢው የሚስተዋሉ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለይቶ በትኩረት መፍታት የወቅቱ አንገብጋቢና የአመራር ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አንስተው ጥያቄዎችን ለመፍታት በቀጣይ ህዝቡን በማሳተፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩም አንስተዋል።

በመጨረሻም የትራንስፖርት አገልግሎት ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ የመብራትና ውሃ አገልግሎት ያለ በቂ ምክንያት መቆራረጥ፣ በሸቀጦች ላይ ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እና ሌሎች የመሳሰሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ጠንካራ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *