








የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የግማሽ አመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የድጋፍና ክትትል ግብረ-መልስ መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የአፈጻጸም ሪፖርት እና ቢሮው በ156 ትምህርት ቤቶች ያደረገው የድጋፍና ክትትል ግብረ-መልስ ሪፓርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል በአደረጃጀት እየተሰራ ያለውን ሁሉን አቀፍ ተግባር ወጥነት ባለው መልኩ በሁሉም የክልሉ አከባቢ ማስቀጠል እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል።
ቀጣይነት ባለው መልኩ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በማሳደግ የትምህርት ቤቶች የደረጃ ማሻሻያ ሥራ ማጠናከር እንደሚገባ ያነሱት ተሳታፊዎቹ ከመደበኛ የመማር ማስተማር ተግባር ጎን ለጎን በገቢ ማመንጫ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ተግባራት አበረታች ነው ብለዋል።
የመምህራን ልማት ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ያነሱት ተሳታፊዎቹ፥ አጠቃላይ የትምህርት ልማት ሥራዎች ውጤታማነት ለማረጋገጥ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት መታከል እንዳለበትም ተናግረዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ሀሳብ የሰጡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የቢሮው ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፥ ተቋማዊ አሰራር በማጠናከር የተጀመረውን የትምህርት ልማት ሥራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ለትምህርት ዘርፍ ስኬትና ውድቅ የዘርፉ አመራር ባለቤት ነው ያሉት አቶ አልማው ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የበጀት ዓመቱን የትምህርት ተግባራት በላቀ ደረጃ መፈጸም ይገባናል ብለዋል።
ከመምህራንና የትምህርት ቤት አመራር ጋር ቀጣይነት ያለውን ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት መፈጠር እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ አልማው የመምህራን ልማት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ መሠረት እንደኾነ ጠቁመዋል።
በመደመር መንግሥት በትምህርት ዘርፍ እምርታ ለማረጋገጥ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የትምህርት ዘርፍ አመራርና ባለድርሻዎች መዘጋጀት እንደሚገባም አቶ አልማው በአጽንኦት አሳስበዋል።
የሚጥሙ ጊዜያዊ ማነቆዎችን በጋራ በመፍታት ለትምህርት ልማት ሥራ በቁጭት መነሳት እንደሚገባ ያስገነዘቡት የርዕሰ መስተዳድሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ደነቀ ማሞ በዘርፉ የመጡ አውንታዊ ለውጦችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ምቹ የሥራ አከባቢ መፈጠር ይገባል ያሉት አቶ ደነቀ፥ በክልሉ በትምህርት ልማት ቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
