




ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችና የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ለመከላከልና ለማስቆም የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የኢፌዲሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሒክማ ኬይረዲን በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ከለውጡ ወዲህ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን በማሳደግ ደረጃ ለውጥ መመዝገቡንና በተለይም የሴቶችን ኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ፖለቲካ ተሳትፎ ከማሳደግ ረገድ ባለፉት 7 ዓመታት መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦች መ መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ፣የህፃናት መብትና ደህንነት ከማስከበር አኳያ በተሰሩ ስራዎች በርካታ ለውጦች መጥተዋል ሆኖም ግን አሁንም የህፃናት ህገወጥ ዝውውር እና ጉልበት ብዝበዛ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን ከመከላከልና ከማስቆም አኳያ ብዙ መስራት የሚጠበቅበት በርካታ ተግባራት እንዳሉም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ የበለጠ እንዲጨምር እያደረገ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ገልፀዋል ፡፡
በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል እና ለማስቆም በሚደረገው ተግባር ላይ ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ክብርት ወ/ሮ ሒክማ አሳስበዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ የሴቶችና ህፃናት ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ከሚገቱ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛዉ የኃይል ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መሆናቸውን አንስተው እነዚህን ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል የሴቶችንና የህፃናት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል እንደክልል በርካታ የፖሊሲ፣ የህግ ማዕቀፎችና የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በክልሉ ከፍትህ አካላት፣ ከህዝብ ምክር ቤት ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎችን መስራት ችሏል፡፡ በዚህም በተወሰኑ የጥበቃ አይነቶች ላይ የመቀነስ ሁኔታዎች ይታያሉ ብለዋል፡፡
በሴቶች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጾታዊ ጥቃት ከስነ ልቦና ጫና በተጨማሪ በጤናቸው ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ ጥቃቱን ከመከላከል ባለፈ የጥቃቱን ሰለባዎች እንዲያገግሙ የማድረግ ስራም መሰራት አለበትም ብለዋል።
በቀጣይ በሴቶች የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትን በመከላከል ውጤቱ ወደ ሚፈለገው ደረጀ ለማድረስ የትብብርና ቅንጂታዊ አሠራሮችን በመፍጠር ሁሉንም አይነት ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በመድረኩ የተለያዩ ሰነዶች እየቀረቡ ሲሆን በቀረቡት ሰነዶች ላይ ውይይት በማድረግ እና ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
