የተጀመረው የሚዲያ የመስክ ምልከታ እውነታን ለህዝብ ገልጦ ለማሳየት ዕድል የሚሰጥ ነው ሲሉ የሚዲያ ባለሙያዎች ተናገሩ።

Spread the love

ባለሙያዎቹ ይህን ያሉት በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ እየለማ የሚገኘውን የበልግ እርሻ የመስክ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት ነው።

በክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባዘጋጀው የሚዲያ መስክ ምልከታ ሀገር አቀፍና የክልል ሚዲያ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ።

ከተሳተፉት ሚዲያዎች መካከል ጋዜጠኛ ቀደሰ ተክሌ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የመጡ ሲሆን እየተከናወነ ያለው የበልግ እርሻ አርሶአደሮችን ራሳቸውን ለመለወጥ የሚያደርጉትን ጥረት ይበልጥ አጉልቶ ያሳየ ነው ብለዋል ።

አሁን ላይ የታየው የበልግ አዝመራ የተሻለ ምርት እንደሚገኝበት እና ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያበረታታ ነውም ብለዋል ባለሙያው።

እየተከናወኑ ያለው የግብርና ልማት ስራ የአርሶአደሩን ተስፋ የሚያለመልም የሚጠበቀውንም ውጤት የሚሰጥ ስለመሆኑ የተናገሩት ደግሞ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ ተስፋዬ ምሬሳ ናቸው ።

በሌማት ትሩፋቶች ፣በግብር በልግ እርሻ አሁን ላይ የሚታየው የምርት አያያዝ የተሻለ ውጤት እንደሚገኝበት አመላካች ነውም ብለዋል።

ሌላኛው በሚዲያ የመስክ ምልከታ ተሳታፊ የሆኑት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ሰለሞን ባረና በመሬት ላይ የሚታየው የበልግ አዝመራ ለአርሶአደሮች ተስፋን የሰነቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚዲያው የአርሶአደሩን የተጠቃሚነት እውነታውን በመግለጥ በሌሎች አርሶአደሮች ተሞክሮው እንዲሰፋ የድርሻቸውን ሊወጣም ይገባል ብለዋል ።

በጉብኝቱ የተሳተፉት የደቡብ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ጦያር ይማም በበኩሉ በአርሶ አደሮች ማሳ ወርደው የተመለከቱት የበልግ ማሳና የሌማት ትሩፋት ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸው በዘገባ ሥራ አውጥተው በማሳየት ለሌሎች ተሞክሮ ለማጋራት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኛ ይታወቅ አስራት በበኩሉ መረጃ ላይ የተመሰረተ ስራ ለማስራት አቅም የሚሆን ጉብኝት መሆኑን ጠቅሷል።

በጉራፈርዳ ወረዳ ኩጃ ቀበሌ በአርሶአደሮች እየለማ ያለው የበልግ እርሻ በአካባቢው የተረጋጋ ሰላም የመኖሩን ሚስጢር አጉልቶ ያሳየ ለአርሶአደሮች ተስፋን የሰነቀ ነው በማለትም ጋዜጠኞች ተናግረዋል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *