በበጀት ዓመቱ 470 ቶን ቡና ወደ ማዕከላዊው ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

Spread the love

በወረዳው ከቅርብ ዓመታት በፊት የቡና ልማት ብዙም ያልተለመደና ከ600 ሄክታር ያልበለጠ የጫካ ቡና መኖሩን በማስታወስ አሁን በተሰጠው ትኩረት ከ10,400 ሄክታር በላይ ማሳ በቡና መሸፈኑን የጣሎ ወረዳ ግብርና ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽህፈት ኃላፊ አቶ አፋወርቅ አደመ ገልጸዋል።

በወረዳው አሁን በሁሉም ቀበሌዎች ማልማት የተጀመረ መሆኑን በመጥቀስ ከዚህ ውስጥ አራቱ ቡናን ስፔሻላይዝ በማድረግ የሚያመርቱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ቡናን በብዛትና በጥራት በማልማት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ አፋወርቅ በበጀት ዓመቱ 5ሺ ቶን ቡናን በማሰባሰብ 470 ቶን ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።

ከዚህም ከ3400 ቶን በላይ ምርት አሁን መሰብሰቡንና 347 ቶን በላይ ቡና ደርቆ ወደ መጋዘን መግባቱን ጠቁመዋል።

ምርታማነት ማሻሻያ ፓኬጅን ከመጠቀም አንጻር ቡናን በክላስተር ማልማት፣ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና መሰጠቱ፣ ከ155 ሄ/ር በላይ ቡና መጎንደሉን፣ የኮምፖስት ዝግጅት እና ሌሎች ምርታማነትን የሚጨምሩ ተግባራት መከናወኑን ገልጸዋል ።

በግብይት ሂደት ጥራትንና የዕዝ ሰንሠለትን ጠብቆ ወደ ገበያ ከማቅረብ አንጻር ህገወጥነትን የመከላከል፣ 4 አቅራቢ ነጋዴዎችን ማዘጋጀት፣2 እሸት ማጠቢያ ኢንዱስትሪ መቋቋሙ፣ የተሻለ የግብይት ማዕከል በወረዳው መታጠሩን አብራርተዋል ።

በወረዳው በአርሶአደሩ ማሳ ከሚለማው ቡና በተጨማሪ የግል አልሚና ማህበራት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ዘርፉን ለማበረታታት ወረዳው ከሰጠው 116.8ሄ/ር ውስጥ በ2002 ዓ/ም ጀምሮ ወደ ስራ በመግባት 96 ሄክታርን በማልማት ላይ ያለው የብ አግሮ ቡና ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው።

ከተተከለው ውስጥ 63 ሄክታር አሁን ምርት እየሰጠ መሆኑን ያነሱት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ አስራት በቀለ ከማልማቱ ጎን ለጎን ምርታማነትን ለመጨመር 25 ሄክታር ጉንደላ ስራና 8ሄክታር ነቅሎ ተከላ መደረጉን ገልጸዋል።

በያዝነው ዓመት 1398 ኩንታል ቀይ እሸት ቡና ለማግኘት ታቅደው እየተሰራ ሲሆን ከዕቅዱ 130% መሳካቱን ጨምረው ገልጸዋል ። እስካሁን 937 ኩ/ል ደርቆ ወደ መጋዘን መግባቱን ተናግረዋል።

የለማው ቡና ወደ አረብ ኢምሬትስ በመላኩ የተሻለ የገበያ ትስስር መፈጠሩንና ገቢ ማግኘቱን የገለጹት አቶ አስራት 22 ቋሚና ከ300 እስከ 400 ለሚሆኑት ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ ዕድል እየተፈጠረላቸው መሆኑን ጨምረው አንስተዋል።

በመጨረሻም ድርጅቱ በዞኑ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች እርሻን ማስፋፋት ላይ እየሰራ መሆኑን አንስተው መንግስት በቦንጋ ከተማ ቦታ ካመቻቸ ዘመናዊ የቡና ማበጠሪያ በማዘጋጀት ቡናውን ቀጥታ ኤክስፖርት ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *