




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት በበሸካ ዞን የዘመናዊ ቡና ልማት ኢንቬቲቭ ማስጀመሪያና ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በቴፒ ከተማ እየተካሄደ ነዉ።
የንቅናቄ ዓላማ በዞኑ ያለውን ሰፊ የቡና ልማት አቅም በመጠቀም፣ አርሶ አደሩ ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የቡና ልማት እንዲያከናውን ለማስቻል መሆኑ ተገልጿል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለፁት፣ የቡና ልማት ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል።
ይህ ንቅናቄ አርሶ አደሩን ካለበት የባህላዊ አሰራር ወደ ዘመናዊና ውጤታማ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያሸጋግር ቁልፍ ኢኒሼቲቭ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢኒሼቲቩ ዓላማው ምርትን መጨመር ብቻ ሳይሆን፣ የቡና ጥራትን በማስጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንደሆነ ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ይህም ለሀገር የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
የቡና ልማቱ እንደ አንድ ትልቅ የኢኮኖሚ ንቅናቄ ተወስዶ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በከፍተኛ ትጋት ከተመራ የዜጎችን ህይወት በአጭር ጊዜ መለወጥ እንደሚቻልም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሸካ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ዓለሙ በበኩላቸው ሸካ ዞን ለቡና ተስማሚ የአየር ንብረትና ለም አፈር ያለው ቢሆንም እስካሁን ያለው ምርታማነት ከሚፈለገው ደረጃ አልደረሰም ብለዋል።
በመሆኑም ይህ አዲስ የዘመናዊ ቡና ልማት ኢኒሼቲቭ የዘርፉን ችግሮች በመቅረፍ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የቴፒ ግሪን ኮፊ ስቴት ባለቤት ኢንጂነር ታደሰ አድማሱ የሸካ ዞን ዘመናዊ የቡና ልማት ኢኒሼቲቭን አስመልክቶ በ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በጠብታ መስኖ የሚለማዉን የቡና እርሻን የተመለከተ ማብራሪያ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ባለሀብቱ በንግግራቸው የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለምርታማነት ያለውን ፋይዳ በዝርዝር እያብራሩ መሆኑን የዘገበዉ የሸካ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነዉ።
በመድረኩ ላይ የክልልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
