በበርካታ ዘርፎች የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑን የባቹማ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

Spread the love

በበጀት ዓመቱ ባለፉት 5 ወራት 3 መቶ ወጣቶችን በመደበኛነት ወደ ስራ ማስገባቱን ከተማ አስተዳደሩ ጠቁሟል።

ወጣቶችን በተለያዩ የስራ ዘርፎች በማሰማራት ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ለከተማው ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እንደ ከተማ አስተዳደር ብዙ ተግባራቶች መከናወናቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን የባቹማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አቤል ታደመ ተናግረዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ 5 መቶ ወጣቶችን በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለማሰማራት ታቅዶ ባለፉት 5 ወራት ብቻ 3 መቶ ወጣቶችን በመደበኛነት ማሰማራት ተችሏል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ከ”JHOCCP” ፕሮጀክት በተገኘ የ22 ሚሊዮን የብር ድጋፍ 2 መቶ 66 ወጣቶችን በዶሮ እርባታ፣ በበግና ፍየል ማሞከት እንዲሁም በንብ ማነብ የስራ ዘርፎች ማስገባት መቻሉንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል አንድ መቶ ሺ ብር የቆጠቡ 12 ወጣቶች 1 ሚሊዮን ብር በመበደር በአንድ ኢንተርፕራይዝ ወደ ከብት እርባታ መግባታቸውንም አቶ አቤል ተናግረዋል።

አደይ ከተሰኘ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር 24 ወጣቶችን የያዙ ሁለት ማህበራት በአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግ ስራ መሠማራታቸውን የተናገሩት ከንቲባው በአሁኑ ሰዓት 1ሺ 700 የአንድ ቀን ጫጩት በመንከባከብ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኦሞ ዞን በከተሞች የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል ያሉት የዞኑ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኋላፊ አቶ በላይ አስፋው በበኩላቸው በዚህም ብዙ ወጣቶች እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እየለወጡ ይገኛል ብለዋል።

ይህም በዞኑ ጀሞ፣ ማጂ ቱምና ባቹማ ከተሞች በስፋት እየተሠራ ይገኛል ያሉት አቶ በላይ ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ያለማማረጥ በመሠማራት ለሀገራቸው ልማትና መበልጸግ አሻራቸውን ልያኖሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በባቹማ ከተማ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት አስተር አረዳ፣ አዲማሱ ታደሠና ሳራ ዘካሪያስ በተመቻቸላቸው የስራ ዕድል ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

አሁን ላይ የአንድ ቀን ጫጩት በማሳደግ የስራ ዘርፍ የተሠማሩት ወጣቶቹ የከተማ አስተዳደሩ ያመቻቸላቸውን ዕድል በመጠቀም የነገ ሕይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *