


በዘርፉ ዘላቂ የሆነ ውጤት እንዲመዘገብ ለማስቻል የድርሻቸውን እንደሚወጡ በክልሉ የኮንታ ዞን ነዋሪዎች ገልፀዋል።
የትምህርት ልማት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በመንግስት የተለያዩ የለውጥ ማዕቀፎች ተነድፈው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛል።
ማዕቀፎቹን ለመተግበር መንግስት በየደረጃው ለህዝብ ተሳትፎ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ባለፉት ጥቂት ጊዜያት አመርቂ ለውጦች ማስመዝገብ መቻሉን በኮንታ ዞን በኮንታ ኮይሻና አመያ ያነጋገርናቸው የትምህርት ባለሙያዎች እና ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።
በዞኑ ኮንታ ኮይሻ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት መሠረተ- ልማትን ለማሻሻል በተደረገ ንቅናቄ በህዝብ ተሳትፎ ብቻ 4 የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚነኙ አስታውቀዋል።
በወረዳው ከ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰብ ተሰብስቦ አዳዲስ መማሪያ ክፍሎች የመገንባት፤ ከቆይታ አንጻር ያረጁ ክፍሎች የመቀየር እንዲሁም የመጸዳጃ ቤቶች ግንባታ ሥራዎች መሰራታቸውን የኮንታ ኮይሻ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አረጋ አስፋው ተናግረዋል።



በዞኑ አመያ ከተማም በሚገኘው የአመያ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተገነባ የሚገኘው 16 የመማሪያ ክፍሎችን የያዘ ባለ 3 ወለል ህንጻ ሲጠናቀቅ ለትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሥራ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጠር ተመልክቷል ።
የአመያከተማ ነዋሪዎችም በሰጡት አስተያየት ዞኑ ለትምህርት ቤቶች መሻሻልና ለትምህርት ጥራት መጠበቅ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ፡፡
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ገዝሙ እንደተናገሩት በሂደቱም ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል።
በመንግስትና ህብረተሰቡን በማስተባበር በዞኑ የአመያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ግንባታን የማጠናቀቅ ፤ የኢሞታ አዳሪ ትምህርት ቤት መገንባትና የጪዳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በአዲስ መልክ የመተካት ሥራዎች በትኩረት እንደተሰሩም አቶ ገዛኸኝ አብራርተዋል ፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ በዞኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እየተገነባ ላለው የኢሞታ አዳሪ ትምህርት ቤት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበ ሲሆን በ2016 የትምህርት ዘመን የላቀ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
በደቡብምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በክልሉ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያግዝ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ሥራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ተፈጽመዋል።
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በተደረገው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ሥራ በህብረተሰቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር ተደርጓል ብለዋል አቶ አልማው ፡፡
በክልሉ ከሚገኙ ትምህርትቤቶች ውስጥ 90 በመቶ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 78 ከመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸው፣ የመማሪያ ከፍሎች መፈራረስ ፣የመጻህፍት ዕጥረት እና ሌሎችንም ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ይህንን ለመቅረፍ በህዝብ እና መንግስት የጋራ ትብብር መማሪያ ክፍሎች የማስገንባት፤ የተማሪዎች መማሪያ መጻህፍት የማሳተም እና ሌሎች ግብአቶች የማሟላት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አቶ አልማው ተናግረዋል ፡፡
በየዞኖች የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እና ባለ ልዩ ተሰጥኦ ተማሪዎችን በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ተቀብሎ ለማስተማር እየተደረገ ያለው የሚያበረታታ ሥራ በሁሉም ዞኖች ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል ፡፡
በ2016 የትምህርት ዘመን በሁሉም ትምህርት ቤቶች 845 ሺህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ የማድረግ ስራ እየተሰራ ቢሆንም የእስካሁን የምዝገባ አፈፃፀም ከ50በመቶ ያልዘለለ በመሆኑ እስከ መስከረም 13 2016ዓ/ም ድረስ በርብርብ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል።
በ2016 ዓም መስከረም 14 ቀንም የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ የሚጀመር ሲሆን እስከዛው የመምህራን ውይይትና የትምህርት ሳምንት በተማከለ እየተከበረ እንደሚቆይም ታውቋል።
