







በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሩዝ አምራች አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም በማደራጀት ወደ ተግባር በማስገባት የሩዝ ምርትን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን በዚህም ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።
በክልሉ በካፋ ዞን ጨና ወረዳ ዶሻ ጡጋ ቀበሌ ያነጋገርናቸው አርሶ አደር አየለ አለሙና ገረመው ኃይሌ በወቅቱ ለእርሻ ስራ በማዘጋታቸውና ግብዓት በአግባቡ በመጠቀማቸው በኩታ ገጠም የተዘረው ሩዝ ውጤታማ እያደረጋቸውና የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሠሩ መሆኑን ይገልጻሉ።
በክላስተር 58 አርሶአደሮች ሆነው የመኸር የሩዝ ልማትን በኩታ ገጠም ማከናወናቸው አረም ለማረም፣ ምርት ለመሰብሰብ በጋራ ጉልበታቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
አርሶአደሮች በቂ ግብኣት፣ የባለሙያዎችን ምክር በመጠቀማቸው አሁን ላይ ምርቱ የተሻለ መሆኑን አንስተው በሄክታር 40 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃለፊ አቶ ገዛኸኝ ጋኖ በ201718 የምርት ዘመን 8ሺህ 5 መቶ ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ የመኸር ሰብሎች መሸፈኑን ገልፀዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ በወረዳው ጎታ እና ዶሻ ጡጋ ቀበሌዎች ክላስተር የሩዝ ምርት በሰፊው የሚመረትበትና በዚህ አካባቢ የሚኖሩ አርሶአደሮች ሩዝ ምርትን በኩታ ገጠም በማምረት የሚታወቁና ተጠቀሚ መሆናቸውን ጠቁመው፡፡
በዚህ ዓመት ሩዝ ምርትን በተለየ መንገድ ለማምረት 83 አርሶአደሮችን በኩታ ገጠም እንዲያለሙ በማድረግ ምርጥ ዘርና አስፈላጊውን ግብኣቶች በማቅረብ አሁን ላይ ሙሉ ፓኬጅ ተጠቅመው በመዝራት በማሳ ላይ ቁመቱም ምርታማነቱም ከበፊቱ የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ360 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራው የኩታ ገጠም ሩዝ ከ2600 በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ መሰራቱን አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል፡፡
በወረዳው በጎታ እና ዶሻ ጡጋ ቀበሌዎች የተጀመረውን የሩዝ ምርት በቀጣይ ሻካ እና መካ ወደ ሚባሉ ቀበሌዎች በማስፋት ተጨማሪ የሩዝ ምርት በማምረት ምርታማነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተረፈ ገ/ማሪያም የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀም የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፥ በወረዳው የሩዝ ምርት በኩታ ገጠም በማምረት አርሶአደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
