




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር (E-VOUCHER) ሥርዓት የግብርና ግብዓት ሽያጭ ይፋዊ ሥራ ማስጀመሪያ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በማስጀመሪያው የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደተናገሩት እንደሀገር የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳለጥ በተለያዩ ዘርፎች በተጀመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው።
ይህን ሀገራዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓትን የማሳለጡ ተግባርን በክልላችን ተግባራዊ ለማድረግ ሥራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያብራሩት።
ከዚህም አንዱ የሆነው በክልሉ የግብርና ግብዓት አፈር ማዳበሪያ ሥርጭትና አስተዳደር ሥርዓቱን በማዘመን ወደ ኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር (E VOUCHER) ሥርዓት ለማስገባት በቤንች ሸኮና ካፋ ዞኖች በሶስት ወረዳዎች የሙከራ ሥራ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች ተመዝግቧል ነው ያሉት።
ይህ የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር (E-VOUCHER) ሥርዓቱ የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት እና ዕዳ አመላለስ አስተዳደር ሥርዓቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ የሀብትና ጊዜ ብክነትን የሚያስቀር መሆኑንም ተናግረዋል።
በሙከራ ደረጃ ተጀምረው የተገኘውን ውጤታማ እንቅስቃሴውን የበለጠ በማጠናከር በክልሉ በሁሉም ዞኖች ባሉት በ41 ወረዳዎች ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም የተናገሩት ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ለስኬታማነቱ ሁሉም መረባረብ ይጠበቃልም ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት የግብርና ግብዓት የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት እና አመላለስ አስተዳደር ሥርዓት ባለማዘመኑ ለበርካታ ተግዳሮት ሲዳረግ እንደቆየ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ተናግረዋል።
በክልሉ የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት እና ዕዳ አመላለስ አስተዳደር ሥርዓቱን ከእጅ ንክኪ የጸዳ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር ሥርዓት በቤንች ሸኮ እና ካፋ ዞኖች በሶስት ወረዳዎች የሙከራ ሥራ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመቀናጀት ሥራዎች መስራቱን ነው አቶ ማስረሻ በላቸው ተናግረዋል።
እንደእነዚህ ያሉ የግብርና ዘርፉን የሚያዘምኑ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉም አንስተዋል።
በማስጀመሪያው የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ገርማሜ ጋሩማ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ጨምሮ ሌሎች በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል የግብርና ኮሜርሻያላይዜሽን ክላስተር ማናጀር ተሰማ ሄርባዬ የኤሌክትሮኒክስ ቫውቸር የሚመለከቱ ጉዳዮችን እያቀረቡ ይገኛሉ።
በፍቅር ከበደ
