ባለፉት 5 ወራት የትራፊክ ደንብ በተላለፉ 17 ሺህ 951 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀልና የትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር አስናቀ አፍቴ የትራፊክ አደጋ መከላከልና የታርፍ ቁጥጥር ስርዓቱን ለማሻሻል በርካታ ውጤታማ ተግባራት በማከናወን ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ከዚህ በፊት የታርፍ ቀጥጥሩም ይሁን የትራፊክ አደጋ መከላከሉና የድጋፍና ክትትል ሂደቱ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በርካታ ውስንነቶች ያለው መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ይህንን ለመቅረፍ ባለፉት ስድስት ወራት በቅንጅት በተሰራው ስራ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

ከታርፍ በላይ በላይ ማስከፈልን ማስቀረት፣ የሌሊት ጉዞ ክልከላ እና የትራፊክ ደንብ ጠብቆ እንዲያሽከርክሩ ከማድረግ አኳያ መጠነ ሰፊ ስራዎች መሠራታቸውን አንስተው ይህም ቀጣይነት እንዲኖረው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ለሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች የተለያዩ ምክንያቶች በመንስኤነት የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነር አስናቀ አፍቴ፤ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር ቀዳሚው እንደሆነና ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት፣ ያለብቃት ማረጋገጫ መንዳት እና የእግረኞች ጥንቃቄ ጉድላት እንደሆነም ገልፀዋል።

በዜጎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት እያደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና ለመቀነስ አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባና ተቋማትም ሆኑ ዜጎች በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ጤናማ የሆነ አስተሳሰብ ይዞ የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ደንብና የአሠራር ሥርዓት ጠብቀው፣ ለትራፊክ ባለሙያዎች ተገዢና ታዛዥ ሆነው እንዲያሽከራክሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ህብረተሰቡና ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በክልሉ የትራፊክ ደንብ ጥሰት በሚፈጸምበት ወቅት ጥቆማ በመስጠት ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።

በክልሉ በ2018 ዓ.ም ባለፉት 6 ወራት 151 የትራፊክ አደጋዎች መከሰቱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ መረጃና ኢስታቲክስ ዲቪዥን ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኢንስፔክተር ወንድወሰን ወንድሙ ገልጸዋል።

ከነዚህም አደጋዎች 38ቱ የሞት አደጋ ሲሆን 103 ከባድ የአካል ጉዳት፣7ቀላል የአካል ጉዳት እና 3 የንብረት ውድመት አደጋ የደረሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የወደመው ንብረት በገንዘብ ስተመን 19 ሚሊየን 259 ሺህ 500 ብር የሚገመት የንብረት ክሳራ መግጠሙን አብራርተዋል።

ባለፉት 6 ወራት የተመዘገበው የትራፊክ አደጋ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱን ምክትል ኢንስፔክተር ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡

የትራፊክ ደንብ የተላለፉ 17ሺህ 951 አሽከርካሪዎች ላይ የክስ እርምጃ ተወስዷል ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር ወንድወሰን በዚህም 31ሚሊየን 290 ሺህ 316 ብር ለመንግሥት ገቢ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በክልሉ በየጊዜው አደጋ የሚከሰትባቸውን ቦታዎች ሊየታ በማድረግ ሃዛርድ መብራት ተከላ በካፋ ዞን አካባቢዎች መሠራቱን ጠቅሰው አደጋውን ለመቀነስ ከ1ሚሊየን ለሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰረቱን አንስተዋል።

ኮሚሽኑ በትራፊክ አደጋ የሚከሰተውን የሞት መጠንን በ10 በመቶ ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ኢንስፔክተሩ ለዚህም መጠነ ሰፊ የዘመቻ ስራዎች በትምህርት ቤቶች፣ በገበያ አካባቢዎች እና በሐይማኖት ተቋማት እየተሰሩ ይገኛል ነው ያሉት።

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *