


የሚዛን አማን ከተማ ልማት የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነትና ዘመናዊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብዝኃ ከተሞች አንዷ ሚዛን አማን ከተማ ለቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ከተማ እየሆነች ትገኛለች።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ኢንጂነር ሰሎሞን ሌዊ፤ በመደመር መንግስት እይታ የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ውብ ጽዱና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ስራ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም የሚዛን አማን ከተማን ግንባታ ዘመኑን የዋጀ የኢንቨስተሮችንና የጎብኚዎችን ቀልብ የምትገዛ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በገጠርም ሆን በከተማ ትውልድን ታሳቢ ያደረገ የዲጂታል ልማትን ማፋጠን፣ ጤናማ የመኖሪያ አካባቢዎችን የመፍጠርና መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በከተማዋ ከኮሪደር ልማት ባሻገር በተመረጡ ማዕከላት ስሉጥ ከተማ የ”ስማርት ሲቲ” ግንባታ ለመጀመር የጥናት እና ፕላን ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ሰው ተኮር በመሆን የአኗኗር ዘይቤን ቀለል የሚያደርጉ፣ ዘመንን የዋጁና ትውልድን መሰረት ያደረጉ መሆኑን አንስተው ሚዛን አማን በዚሁ ልክ እየተሰራች ትገኛለች ነው ያሉት።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ፍሬሕይወት ከበደ እና ቤላ ኮይ፤ የሚዛን አማን ከተማ ውበትና ለውጥ የሚታይ መሆኑን ገልጸው ስራዎቹ ከተማዋን ወደ ትልቅ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
በከተማዋ በተለየ ፍጥነትና ጥራት ግንባታዎች እየተከናወኑ እና እየተጠናቀቁ ለአገልግሎት እየበቁ መሆኑን ተናግረው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
