




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ በማጂ ቱም ከተማ አስተዳደር የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ10ሺህ ለሚበልጡ የአከባቢው ነዋሪዎች አግልግሎት የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ በባስኬት ፈንድ ፕሮግራም፤ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃ ልማት ፈንድ በኩል በተገኘ 55 ከመቶ ብድር እና 45 በመቶ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የወጪ መጋራት ድርሻ የተገነባ ሲሆን አጠቃላይ ወጪው 98 ሚሊዮንብር የወጣበት መሆኑ ተመላክቷል።
ፕሮጀክቱ የ4 ምንጭ ግንባታና መልሶ ጥገና፣ የ9.13 ኪ.ሜ ዋና የግፊት መስመር ዝርጋታ ስራ፣ የ21.745 ኪ.ሜ ርዝመት የውሃ ማሰራጫ መስመር ዝርጋታ፣ 4 የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ግንባታ፣6 ቦኖዎች፣ የውሃ አገልግሎት ህንጻ ፣ ሞዳሌ የህዝብ መጸዳጃ ቤት ያካተተ መሆኑም ነው የተገለጸው።
በምረቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ የኢፌዴሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር አስፋው ድንጋሞ (ዶ/ር)፣ የክልሉ የመንግሥት ተጠሪ አቶ ፍቅሬ ማንን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
