

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመስኖ ልማት ኤጄንሲ ከክልሉ ግብርና ቢሮ እና ከኢፌዴሪ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር ላለፉት አምስት ተከታታይ ቀናት በውሃ መሳቢያ ፓምፕ አጠቃቀምና ጥገና ላይ በቦንጋ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ስሰጥ የነበረው የአሰልጣኞች ስልጠና አጠናቋል።
ከክልሉ ስድቱም ዞኖች የተወጣጡ የውሃ መሀንዲሶችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የአሰልጣኞች ስልጠናው በአነስተኛ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ አጠቃቀምና ጥገና ላይ የሚታየውን የክህሎት ችግር በመቅረፍ የመስኖ ልማት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ዓላማ ያደረገ እንደነበረ በማጠቃለያው ተገልጿል።
በስልጠናው የተገኘውን እውቀት ችግር ፈቺ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት የክልሉ የመስኖ ልማት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር እንጂነር አሸናፊ ሽብሬ ሰልጠኞቹ ወደ መጡበት ስመለሱ ሌሎችን በማሰልጠን አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግሯል።
በጽንሰ ሀሳብ እና በተግባር ላይ የተሰጠው ስልጠና በክልሉ በዝናብ ጥገኛ የሆነውን የእርሻ ስራ በመስኖ ልማት ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት የጎላ ሚና እንዳለው የገለጹት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፈ በጥቃቅን ብልሽት የቆሙ የውሃ ፓምፕችን በመጠገን ወደ ስራ ለማስገባት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ባገኙት የተግባር ስልጠና በቂ እውቀት እንዳገኙ የተናገሩት ሰልጠኞች ወደ መጡበት ሲመለሱ በተሰጣቸው የስራ መመሪያ መሠረት ወደ ተግባር ፈጥኖ እንደሚገቡ አስረድተዋል።
በስተመጨረሻም ለሰልጣኞች የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
