




የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ አሊ መሐመድ ኡመር ዛሬ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።
አምባደሳደር ምስጋኑ በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ህዝቦች የማይነጣጠል መፃኢ ዕድል ያላቸው መሆኑን በመግለፅ፤ ሀገራቱ ተባብረው መስራት፣ ችግሮች ሲጋጥሙም ተቀራርቦ መፍትሄ መሻት ይገባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለአንካራው ስምምነት ተግባራዊ መሆን ቁርጠኛ ናት ያሉት አምባሳደር ምስጋኑ፤ የሁለቱ ሀገራት ትብብር ማደግ ለቀጣናው ሰላም እና ዕድገት ወሳኝ እንደሆነም መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ አሊ መሐመድ ኡመር በበኩላቸው፥ ሶማሊያ የአንካራው ስምምነት በተፋጠነ ሁኔታ እንዲተገበር ትሻለች ሲሉ ገልፀዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ መገኘታቸውም ለስምምነቱ ተፈፃሚነት ሀገራቸው ያላትን ዝግጁነት እንደሚያሳይ የጠቀሱት አሊ ኡመር፤ ለሰላም መረጋገጥ እና ለጋራ ዕድገት የሶማሊያ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ባተኮረው የሚኒስትር ዲኤታዎቹ ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደከፈለች አምባሳደር ምስጋኑ አስታውሰዋል።
ሁለቱ አካላት ለግንኙነታቸው መሻሻል አሁን የጀመሩትን ውይይት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ እንዲሁም በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ተቀራርበው እንደሚሰሩ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
