አዲሱን ሪፎርም መሰረት ባደረገ መልኩ በአንድ ማዕከል ዉስጥ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ በአዲሱ ሪፎርም ዕሳቤዎችና በአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በቦንጋ ከተማ ስልጠና ሰጠ።

የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻዉ በመክፍቻ ንግግራቸው እንደገለጹት አዲሱን ሪፎርም መሰረት ባደረገ መልኩ በአንድ ማዕከል ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት እና የአሰራር ስርዓቱን በማሻሻል ከወቅቱ እሳቤ ጋር በማስተሳሰር የተሻለ ዉጤት ማስመዝገብ አለብን ብለዋል።

በሁሉም ቦታ ለሚገኙ የአግልግሎቱ ተጠቃሚዎች ወቅቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ስራዎች ተጠናክረዉ መቀጠል እንዳለባቸዉም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

አሰራሮችን በመዘርጋት ፈጠራ የታከለበት ሪፎርም ለመተግበር እንዲያስችል በሁሉም ኮሌጆችና ተቋማት ለማዳረስ የክህሎቱ ስልጠናው በየደረጃው እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በምክክር መድረኩ የሪፎርም ምንነትና ትርጉም በሚል ርዕስ ሰነዱን ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ ሪፎርም አንድን ነገር ለማሻሻል በሁሉም ተቋማት ላይ ለዉጦችን የማድረግ ሂደት የሚያመልክት መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ተስፋዬ አክለዉ የተለያዩ የሪፎርም ዘርፎች ቢኖሩም በዋናነት ሪፎርሞች በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ተቋማዊ የአሰራር ሂደት ላይ ያተኮረ ማሻሻያ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን አየለ በበኩላቸዉ የተቋማት ግንባታ ለስራ ፈላጊዎችና ኢንተርፕራይዞች የሚሰጡ ህጋዊነትን የማስፈን እና የመንግስታዊ ድጋፍ አገልግሎቶችን በተቀናጀ መልኩ ከአንድ ስፍራ በአንድ አስተባባሪነት ዜጎች አገልግሎት ማግኘት ያስችላል ብለዋል።

አቶ ሰለሞን አክለዉም ከወረቀት የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት አዲሱን እሳቤ በአንድ ማዕከል ዉስጥ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዉ ስልጠናዉ ከዞን እስከ ወረዳ መዋቅሩ ተዘርግቶ በቀጣይነት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በመድረኩ አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸዉ አዲሱን አሰራር ለመተግበር የሰዉ ሀይል እጥረት መኖሩን ገልጸዉ ወደፊት ያልተሰሩ ተግባራቶችን በመለየት ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲያስችል ከስልጠናዉ አቅም ማገኘታቸዉን ተናግረዋል።

በመጨረሻም በቀረበዉ ሰነድ በተሳታፊዎች ሀሳብና ጥያቄ ተነስቶ በሚመለከታቸዉ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ መድረኩ ተጠናቋል።

በፀሀይ በላቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *