





አገር ተረካቢ ትውልድ በመጤ ባህሎች እንዳይበረዝ በትኩረት መሰራት ይገባል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ያለመ አገር አቀፍ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በድሬዳዋ ተካሂዷል።
መርሃግብሩ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና የእግር ጉዞ ተጀምሯል።
ሚኒስትሯ፥ በዚህ ወቅት ብዝሃ ማንነቶቻችንና ዘመን ተሻጋሪ እሴቶቻችንን በመጠበቅና በማጎልበት ለአገር እድገትና የብልጽግና ጉዞ ማሳኪያ እንዲውሉ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ጠቃሚ እሴቶቹን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር ወጣቶችን ተጠቃሚ በማድረግና ለአገር ግንባታ እንዲውሉ ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በተለይም አገር ተረካቢ ትውልድ በመጤ ባህሎች እንዳይበረዝ በትኩረት መሰራት ይገባል ብለዋል።
ወጣትነት አዳዲስ ነገሮች ሁሉ የሚሞከሩበት የዕድሜ ወቅት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ወጣቱ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዳይጎዳ በመከላከል ብቁና አሸናፊ ትውልድ ለመገንባት መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ በበኩላቸው፥ በአስተዳደሩ ወጣቶች ጊዜያቸውን በስፖርትና በንባብ እንዲያሳልፉ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ ነው።
በድሬዳዋ የተጀመረው አገር አቀፉ የንቅናቄ መርሃ ግብርም ወጣቶችን ከመጤ ባህል ወረርሺኝ ለመጠበቅ እንዲሁም በዘርፉ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ለማስቻል ነው ብለዋል።
ዛሬ በድሬዳዋ የተጀመረው አገርአቀፍ የንቅናቄ መርሃግብር በሁሉም ክልሎችና ከተሞች የሚካሄድ መሆኑም በወቅቱ ተገልጿል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
