
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ተግባራትን ለማሳካት እንዲቻል ከ2 ሚሊዮን 443 ሺህ 600 ብር በላይ የሚገመት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ መፈጸሙም ተገልጿል ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የወሳኝ ኩነቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ደነቀ እንደገለጹት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች ወደ ድጅታል ምዝገባ ሥራ /Online / ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ባሉ መዋቅሮች ከ700 በላይ ቀበሌዎችን በድጅታል ምዝገባ ስራ ማስገባት መቻሉን ኃላፊው አስረድተዋል ፡፡
የሲቪል ምዝገባና ቫይታል ስታትስቲክስ መረጃ ለጤና፣ ለትምህርት እና ለሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶች እቅድ ዝግጅት፣ ለፖሊሲ ቀረጻ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ለማመንጨት መሠረት መሆኑንም አቶ ሰለሞን ደነቀ ተናግረዋል ፡፡
በወሳኝ ኩነት ከሚመዘገቡት ውስጥ አንዱ ልደት ሲሆን ኩነቱ እንደተከሰተ ወዲያውኑ በመመዝገብ ዜጎች ማንነታቸውን የሚያረጋግጡ ህጋዊ ሰነዶችን በማስገኘት ዕውቅና እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን የሞት ምዝገባ ሰነዶች ውርስን፣ የባለቤትነት መብትን፣ የመድን ዋስትና እና እንደገና ለማግባት የሚያስችለውን ህጋዊ መብቶችን እንደሚያጎናጽፍ አቶ ሰለሞን ደነቀ አስረድተዋል ፡፡
የጋብቻ እና የፍቺ ምዝገባ ሰነዶች ለቤተሰብ መብት ጥበቃ፣ ለንብረት ክፍፍል፣ ለህጋዊ ወራሽነት፣ ለቤተሰብ ድጎማ እና እንደገና የማግባት መብቶችን የሚያጎናጽ ማስረጃዎች መሆናቸውንም አቶ ሰለሞን ደነቀ ገልጸዋል ፡፡
በመሆኑም ከዚህ በፍት የነበረው የማኑዋል ምዝገባ ሥርዓትን በማሻሻል የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓትን ዲጂታላይዝ ማድረግ ወቂታዊና ታምኖበት በክልሉ ዉስጥ ካሉ ቀበሌያት ዉስጥ ከ700 በላይ ቀበሌዎች ወደ ዲጂታል ምዝገባ እንድገቡ ተደርጎዋል ሲሉም አቶ ሰለሞን ደነቀ አብራርተዋል ፡፡
ይህን ተግባር ለማሳካት እንዲቻል ወደ 2 .5ሚሊዮን በሚጠጋ ብር የተለያዩ ቁሳቁሶች ተገዝተዉ ለየመዋቅሮች ስርጭት ማድረግ ተችሏልም ብለዋል ፡፡
በዚህም መሰረት የወሳኝ ኩነት የምዝገባ መረጃዉ ወደ ፌደራል መረጃ ቋት በወቅቱ እንዲደርስና መረጃዉ ለተፈለገበት ዓላማ እንዲዉል ከማድረግ አንጻር የጎላ አስተዋጽኦ ስላለው የዲጂታል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ከማኑዋሉ በተሻለ ሁኔታ ጊዜ፣ ጉልበት፣ ወጪ ቆጣቢ መሆኑና፣ በተጨማሪም ወቅታዊ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አፈጻጸምን ከፍ እንደሚያደርግ ያግዛል ሲሉ በመግለጫቸው አክለዋል፡፡
የወሳኝ ኩነቶች ዘርፍ ኃላፊ የዲጂታል ተግባርን በዕዉቀትና በጥራት እንዲሰራ የክልል፤የዞን ፤የወረዳ፤የከተማ አስተዳደር እና የቀበሌ የመዝገብ ሹሞችን ጨምሮ ከ350 በላይ ሰዎች ስልጠና የተሰጣቸው መሆኑንና ስልጠና ላልወሰዱ መዝጋቢዎች በየደረጃው ካሉ መዋቅሮች የተወጣጡ የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች በየመዋቅሮቻቸው ስልጠና እንዲሰጡ ተደርጓልም ብለዋል ፡፡
ሁሉም ሰው የሚታወቅባትን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የምዝገባ ሥራ አፈጻጸምን ለማሳደግ መስራት ይገባዋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡
በታጠቅ አበበ
