በክልሉ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር የተሰሩ አመርቂ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖር የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚሻ ተገለጸ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬትጨየ2017 በጀት ዓመት ዓመታዊ አፈጻጸምና እና የ2018:ዓ/ም 1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ በሚዛን አማን እያካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኃይሌ ዘውዴ ክልሉ አዲስ ከመሆኑ አንጻር ተቋሙን የሰው ኃይልን ከማሟላትና አቅምን ከመገንባት ብዙ ተግባራት መከናወኑን አንስተዋል።

አክለውም በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ተጋላጭ ማህበረሰብ ክፍሎችን ላይ የባህሪ ለውጥ ከማምጣት ከመለየት ከመመርመርና ከመምከር ብዙ ስራ መከናወኑን አንስተዋል።

ለረጅም ዓመታት ዝቅተኛ አፈፃፀም ሲመዘገብበት የነበረው የቫይረስ ምርመራ አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት 82% ማከናወን መቻሉንና ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ውስጥ 38 የጤና ተቋማት የፀረ ኤች.አይ.ቪ ህክምና የሚሰጡ መኖሩን ያነሱት አቶ ኃይሌ 9020 ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ህክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት ተቋማትን በማስፋፋት ህክምናውን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በኤችአይቪ ኤድስ የተያዙ ህፃናትን ለይቶ መድኃኒት ከማስጀመር አፈጻጸሙ 79% ላይ መሆኑን ገልጸዋል ።

በመሆኑም በበጀት ዓቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠልና ጉድለቶችን ለማረም የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚሻ አቶ ኃይለ አሳስበዋል ።

በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ኤች አይ ቭ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ከሰሪ ከተቀመጡ ሀገራዊ ግቦች አኳያ 3ቱ 95 ግቦች አንጻር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መቆየቱን አንስተዋል።

የኤችአይቪ ምክክርና ምርመራን በተመለከተ 200,000 ቁልፍና ቅድሚያ የሚሰጣቸው የማ/ሰብ ክፍሎችን የተለያዩ የምርመራ ስልቶችን በመጠቀም ለመመርመር ታቅዶ 92% ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል ።

በበጀት ዓመቱ 967 አዲስ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን ማግኘት የተቻለ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 45ቱ ከ15 ዓመት በታች ሲሆኑ የህክምናና ክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ የሆኑት አቶ ደነቀ ማሞን ጨምሮ የክልሉ ጤና ቢሮ የማኔጅመንት አባላት፣ የዞን መምሪያና የወረዳ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *