






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከአልሚ ባለሃብቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ክልላዊ ኢንቨስትመንት ፎረም በሚዛን አማን ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥ በክልሉ በርካታ አልሚዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት ሀገራዊና ክልላዊ ኢኮኖሚ እየደገፉ ይገኛል።
ከክልሉ ምሥረታ በፊት ዝቅተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደነበረ ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አሁን ላይ በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በእጅጉ መጨመሩን ገልጸዋል።
ለዚሁ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መጨመር መንግሥት ለግሉ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት እንዲሁም የሚስተዋሉ የቢሮክራሲ ማነቆዎችን በቅርበት መፍታት በመቻሉ ነው ብለዋል።
የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ መሪ ተዋናይ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት ይደግፋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አልሚዎችም የተፈጠሩ መልካም ዕድሎችን በተገቢው በመጠቀም ምርታማነታቸውን ማላቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የግሉ ዘርፍ አልሚዎች በበኩላቸው በተሰማሩበት መስክ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠር፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማሳለጥ እንዲሁ በፈጠሩት ሀብት የአከባቢውን ልማት የመደገፍ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ዶ/ር ነጋሽ አሳስበዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ለመሳብ በተሰሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የገለጹት የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ በዚህም የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመሩን ተናግረዋል።
በክልሉ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠር፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም መገንባት፣ የቴክኒክና ድጋፍ እንዲሁም የመሬት አቅርቦት በማሳለጥ የዘርፉን እምርታ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መኾኑንም ነው አቶ ታሪኩ የገለጹት።
በክልሉ ፍትሀዊና በውድድር ላይ የተመሠረተ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲኖር በማድረግ የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ሚና ለማሳደግ ቢሮው በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ነው አቶ ታሪኩ ያብራሩት።
ለዘርፉ ውጤታማነት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ቀጣይነት ባለው መልኩ በየደረጃው የመፍታት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆሙት አቶ ታሪኩ ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
