




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት የከተማ መሠረተ ልማትን በማጠናከር ረገድ ውጤታማ ሥራዎች መከናወኑን የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገልጿል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ወራት ለከተሞች መሠረተ-ልማት ግንባታ ከ81.3 ሚሊዮን በላይ ሀብት ከሕብረተሰቡ በገንዘብ፣ በጉልበትና በዓይነት በማሰባሰብ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ነው የቢሮ ኃላፊው ኢንጂነር የማታለም ቸኮል የተናገሩት።
በስድስት ወራቱ 125.33 ኪሎሜትር የከተማ መንገድ ከፈታና ጠረጋ እንዲሁም 33.8 ኪሎሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ መከናወኑንም አስረድተዋል።
ኢንጂነር የማታለም ቸኮል 29.88 ኪሎሜትር የከተማ የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ 26.14 ኪሎሜትር የመንገድ መብራት አገልግሎት ዝርጋታ በተጨማሪ የጎርፍ መውረጃ ዲቺ ቦይና ክትር 6.382 ኪሎሜትር እንዲሁም 114.47 የጠጠር መንገድ ጥገና ሥራ ተከናውኗልም ብለዋል።
የክልሉ ከተሞች ለነዋሪዎች ለመኖሪያ ጽዱና ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምቹ እንዲሆኑ ከመንግስት በጀት በተጨማሪ ሕብረተሰቡን በማስተባበር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ ባለፉት ወራት 8.3 ኪሎሜትር የኮሪደር ልማት መሰራቱን ጠቅሰው ሥራዉ የእግረኛ መንገድ፣ አረንጓዴ ልማትና ሌሎች የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ያካተተ ስለመሆኑንም ጠቁመዋል ።
ለከተሞች መሠረተ-ልማት ሥራ ሕብረተሰቡ የሚያደርገው የገንዘብ፣ ገልበትና ቁሳቁስ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ የከተሞች የልማት እንቅስቃሴ እየተነቃቃ ይገኛልም
ብለዋል።
ሕብረተሰቡ ለከተሞች መሠረት ልማት ሥራ እያደረገ ያለውን ሁሉዓቀፍ ተሳትፎ እንዲያጠናክርም የጠየቁት ኃላፊው ከተሞች ለልማት ሥራዎች ሀብት መድበዉ በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ ሥራዎችን አጠናቅቀዉ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ከመሸጋገር አኳያ የሚታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት እንዲያርሙም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በፍቅር ከበደ
