የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት ለዜጎች ምቹና አስተማማኝ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የትራንስፖርት ዘርፍ አብይ ግብረ-ሃይል የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የግብረ-ሃይሉ አባላት በሰጡት አስተያየት መድረኩ ችግሮችን በጋራ በመለየት በቀጣይ መፍትሔ ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑንና ለዚህም ከመናኸሪያ ጀምሮ የሚሰሩ የዘርፉን ተግባራት በአሠራር ስርዓት በመስራት ለውጥ ለማምጣት በመቀናጀት ችግሮቹን ለመፍታት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ንጉሴ ወ/ጎርጊስ፤ የትራንስፖርት ዘርፍ በእያንዳንዱን ዜጋ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ሚና የሚጨወት መሆኑን አንስተው በዚሁ ዘርፍ ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት ምቹና አስተማማኝ እንዲሆን መንግሥት በኩል ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የዜጎችን ሞትና የአካል ጉዳት በመቀነስ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ንጉሴ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የክትትልና ቁጥጥር ሂደትን ማጠንከር፣ በስራው ዜጎች ግዴታቸው በብቃት እንዲወጡ ማስቻል እና ሚዛናዊ የሆነ አገልግሎቶችን በትኩረት መስራት እንዳለበትም አንስተዋል፡፡

በትራንስፖርት ዘርፍ በሚደረጉ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎች ላይ ሰፊ ችግሮች መኖራቸውንና ይህንን በመፍታት ወጤታማ የሆነ ተግባር ለማከናወን በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስቤ ሻዎኖ፤ የትራንስፖርት ዘርፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚወስን ዘርፍ በመሆኑ ይህንን ወጤታማ ለማድረግ ባለድርሻ መስሪያቤቶች የየራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚጠበቅ ተናግረው በክልሉ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ የተጀመረው ህጋዊና አስተዳዳራዊ እርምጃዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትልና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸብር ኢካሎ ለግብረ-ሃይሉ በቀረቡት የመወያያ ሰነድ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ 471 የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ የስምሪት መስመሮች እንዳሉ እና በዚህም በዓመት 12 ሚሊየን ለሚጠጉ ዜጎች የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት ዘርፉ ህገ ወጥ ስራዎችን አለማስቆም፣ የጥገና አሰራር ደረጀ ለማሻሻል ፍቃደኛ ያለመሆን፣ የአሽከርካሪዎች ማሣልጠኛ ተቋማት ደረጀ መውረድ፣ ያልተመረመሩ ተሽከርካሪዎች ቦሎ መለጠፍ እና መሰል ችግሮች ለዘርፉ ተግባር ማናቆ መሆኑንና ይህንንም ለማረም በጋራ ዕቅድ መመራትና ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *