





በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል “የመሐሉ ዘመን ወጥመድ መሻገር “በሚል መሪ ሀሳብ የአመራር የዉይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው ።
የለውጥ ሽግግር ዘመን ፈተናዎችን በውል በመረዳት ይህንን የሚመጥን የሐሳብ ጥራትና አንድነት በመፍጠር ፣ በትጋትና በቁርጠኝነት ተግባራትን መፈጸም ያስፈልጋል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።
የለውጥ ሽግግር ዘመን – መንግሥት በሁለት እግር የሚቆምበት፣ የተለያዩ ኃይሎች ወደ ተመሳሳይ ዓላማ በመሰባሰብ አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት የሚፈጥሩበት እንደሆነም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የለውጥ ሽግግር ዘመን ፈተናዎችና የሥልጣን ፉክክር የሚቀንስበት፣ የሕዝብ ስሜት በውል በመረዳት ተቋማዊና መዋቅራዊ አቅሞችን በመገንባት የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምንተጋበት ዘመን ነው ሲሉም ተናግረዋል ፡፡
አሁን የምንገኝበት የለውጥ ምዕራፍ ነባሩን ሐሳብና ኃይል በማክሰም እና አዲሱን የለውጥ ሐሳብና ኃይል በመትከል መካከል ያለ የሽግግር ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
ለውጡን ወደ ተሟላ ወጤት ለመቀየር የተፈጠረውን አንጻራዊ ሠላምና አስተማማኝ ህልውና፣ ኢኮኖሚያዊ መሠረትና መደላድል እንዲሁም ውስጣዊና ውጫዊ አስቻይ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመጠቀም ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር አለብን ስሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡
ሀገራዊ አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት፣ በሀገራዊ ምክክር ዐውድ አማካኝነት ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ይገባልም ስሉም ገልጸዋል።
ዲሞክራሲን በማጽናትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በማድረግ ለውጡን ወደ ተሟላ ውጤት መቀየር እንደሚያስፈልግም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ፡፡
የመሐል ዘመን ወጥመዶችን በመሻገር ለውጡን ከመትከል ወደ ላቀ ውጤት መቀየር የሚቻለው
መላው ሕዝባችን ከምን ጊዜም በላይ በማንቃትና በማደራጀት እንደሆነም ተናግረዋል ።
ሕዝብ የሠላም ዘብ እንዲሆን በማድረግ
የድህረ እውነት ፈተናዎችን በጠንካራ ተግባቦት ማሸነፍ የልማት ሥራዎችን በላቀ ብቃት በመፈጸም
የህዝብ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የሕዝብ እርካታን በማረጋገጥ በመሆኑ አመራሩና አባሉ በልዩ ቁርጠኝነት መሥራት ያስፈጋል ብለዋል።
የውስጥ ጸረ ሠላም ኃይሎች በገጠማቸው ችግር ምክንያት የሚከተሏቸውን የትግል ስልቶችን በውል መረዳትና ለዚህ የሚመጥን ቅድመ ዝግጅት በሁሉም ደረጃ ማድረግም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እስከአሁን ባገኛናቸው ድሎችና ባሳካናቸው ውጤቶች ሳንኩራራ ለአዲስ ፈተና መዘጋጀት፣ ለተጨማሪ ስኬት መትጋት በአጠቃላይ ቀጣይነት ያለው ለውጥና ዕድገት ለማስመዝገብ መጣር አለብን ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል ፡፡
ስኬት ከሚወልደው መዘናጋትና በሂደትም ከሚያስከትለው ውድቀት በመጠንቀቅ ሁልጊዜ ለተደማሪ ስኬት በመትጋት የሕዝብ ተጠቃሚነትን በተጨባጭ ማረጋገጥ ያስፈልጋልሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ፡፡
በዉይይት መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የየዞን አስተባባሪ አካላት ተገኝተዋል ።
በታጠቅ አበበ
