





በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ እንዲያመርት የሚያስችለው የውኒ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ባገኙበት ተመርቋል።
በምረቃው መርሐ-ግብር መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)÷ ባለፋት የክልሉ ምሥረታ ወቅት በክልሉ የሚስተዋሉ የልማት ክፍተቶችን በመለየትና ትኩረት በማድረግ በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን መሰራት ተችሏል ብለዋል።
የተገነባው የመስኖ አውታር የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የቤተሰብ የኢኮኖሚ አቅም የሚያሳድግ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
የአከባቢው አርሶአደሮች ትርፍ በማምረትና ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማላቅ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ አርሶአደሮች ውጤታማ እንዲኾኑ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ተቋማት የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ተግባራት መጠናከር አለበት ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ያረጋገጡት ዶ/ር ነጋሽ የህዝብ ትብብር በሁሉም መስክ መጠናከር አለበት ብለዋል።
የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው በምረቃው ወቅት እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ 2.75 ኪሎ ሜትር የዋና ቦይ እና 2.7 ኪሎ ሜትር የሁለተኛ ደረጃ ቦይ ግንባታን ያካተተ ዘመናዊ የመስኖ መሰረተ-ልማት ነው።
ፕሮጀክቱ በአንድ ጊዜ 144 ሄክታር መሬትን የማልማት አቅም ያለው ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኙ 1,400 የቤተሰብ አባላትን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም፣ ግንባታው በገዛኸኝ ዋጄቦ የውሃ ስራዎችና ጠቅላላ ተቋራጭ የተከናወነው ይህ ፕሮጀክት፤ አርሶ አደሩ ዘመናዊ አሰራርን በመከተል ምርታማነቱን እንዲያሳድግና የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የአከባቢው ነዋሪዎች የመስኖ አውታሩ ቀጣይነት ያለውን አግልግሎት እንዲሰጥ በመጠበቅ፣ በማህበራት ተደራጅተው በተገቢው መገልገል እንዳለበት ነው የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ያስገነዘቡት።
አርሶአደሮች ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው በአመት ከአንድ ጊዜ በላይ በማምራት የቤተሰብ ብልጽግና እንዲያረጋግጡ የመስኖ አውታር መገንባቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው አቶ ዳዊት የገለጹት።
የአከባቢው አርሶአደሮች ይህን መልካም አጋጣሚ በተገቢው በመጠቀም ዘመናዊ ግብርና ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማላቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመጨረሻም ለፕሮጀክቱ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
