በበጀት ዓመቱ በመሠረተ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተሻለ የተግባር አፈጻጸም ተመዝግቧል። ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢንጂነር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአስፈጻሚ አካላት የ2016 በጀት ዓመት የማጠቃለያ ተግባር አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የዛሬው ውሎ በመሠረተ ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተቋማት ዝርዝር የተግባር አፈጻጸም ቀርቦ ተገምግሟል።

በኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህም አስፈጻሚ ተቋማቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማስፈጸም አቅም እያሳደገ እንደሆነ አመላካች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በግብርናው ዘርፍ የአረንጓዴ አሻራ ዝግጅት፣ የማዳበሪያ ዕዳ አመላለስ እንዲሁም የእንስሳት እርባታን ከሌማት ትሩፋት ጋር በማስተሳሰር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፈጠር የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ የተግባሩን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በቀጣይ ተቋማት በጋራ ጉዳዮች የጋራ ዕቅድ በመንደፍ ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በክልሉ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ኦዲት በማድረግ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ችግር ፈቺ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የኑሮ ውድነት እያባባሰ ያለውን የህገወጥ ንግድና ግብይት ህብረተሰብን በማሳተፍ ከፀጥታ መዋቅር ጋር በቅንጅት መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉን የገቢ አቅም ለማሳደግ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ በተሰራው ስራ የተገኘው ውጤት አመርቂ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በተላይ በገጠር የእርሻ ኢንቨስትመንት፣ የአርሶአደሩ መሬት መጠቀሚያ ግብር እንዲሁም በማዘጋጃ ቤታዊ አግልግሎት የተገኘው ገቢ ቀጣይ ብዙ ከተሰራበት የተሻለ ሀብት የሚገኝበት መሆኑን ያመላከተ እንደሆነም ተናግረዋል።

በአርብቶአደር አካባቢ የቆዩ ነባር ፕሮጀክቶችን በትኩረት ለማጠናቀቅ ልዩ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ የማዕድን ዘርፉን በመደገፍ ህጋዊ የግብይት ስርዓት በማስፈን ከዘርፉ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

በመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ዘርፍ በክልሉ አራት ከተሞች ተግባራዊ የተደረገው የዲጂታል መናኸሪያ አግልግሎት ውጤታማ እንዳይሆን የሚደረጉ መሰናክሎች መፈጠራቸው አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ አጥፊዎች በመለየት በህግ የማስጠየቅ ስራ በፀጥታ መዋቅሩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የግብርና ተግባራት የክልሉን አርሶናአርብቶ አደር ህይወት በተጨባጭ በሚለውጡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ያሳሰቡት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በመሰረተ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የተገኙ አመርቂ ውጤቶችን በማስቀጠል በቀጣይ ከዚህም የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በየደረጃው ያለውን አመራር በማቀናጀት ተገቢው ትኩረት መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኩታ ገጠም እርሻ በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ተግባር ተስፋ ሰጪ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ና የአሲዳማ አፈር የለምነት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።

የህብረት ሥራ ማህበራትን አቅምና አቋም ለማስተካከልም የተጀመረዉ ሪፎርም እየተጠናቀቀ መሆኑን አቶ ማስረሻ ገልጸዋል።

ሌሎች የመድረኩ ተሳታፊ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች በኩላቸው የተመዘገቡ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ቀጣይ ትኩረት በሚሹ በተላይ የግብርና ግብዓት አጠቃቀም፣ የማዕድን ሀብት አስተዳደር እንዲሁም ህገወጥ ንግድና ግብይ መከላከል እንደሚገባ ጠይቀዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *