ሪፖርታዥ



ደን ለሰው ልጆች ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። በተለይ የአየር ፀባይ ሚዛንን ከመጠበቅ አንጻር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በኢንዱስትሪ ማዕበል የተጥለቀለቁ የዓለም ሀገራት ከፍተኛ የተቃጠለ አየር ለተቀረው ዓለም ከማስረከብ ያለፈ ንጹህ አየር ማምረት ላይ ጠብ ያለ ተግባር አሳይተዋል ማለት ግን አይቻልም።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሰፊ የደን ሽፋን ያላት ሀገር ቢትሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ የደን ሽፋን ምጣኔ እየቀነሰ መምጣቱ ግልጽ ነው። ሆኖም እንደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ያሉ በኅብረተሰብ የደን አጠባበቅ ባህል የዳበሩ የሀገራችን ክፍሎች የዓለም ሳንባ ሆነው እያገለገሉ ነው። ይህን ጠብቆ የማቆየትና እና ለትውልድ አስፋፍቶ የማስተላለፍ ተግባር በመንግስት እና በኅብረተሰቡ በጋራ ትብብር እየተሰራ ይገኛል።
ዶክተር ኢንጂነር አስራት ገብረማርያም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን፣አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የክልሉ መንግስት ለተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ትኩረት ከመስጠት አንፃር በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር እየፈጸመ ነዉ።
ደን፣አከባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ በቢሮ ደረጃ ከተደራጀ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ያለው ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና ብዝሃ ህይወት ማልማት፣ መጠበቅና መንከባከብ እንዲሁም ማህበረሰቡ ከተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ በሚሆንበት ሁኔታ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ቢሮው በዋናነት የተፈጥሮ ሀብቱን ከመጠበቅ፣ ከመንከባከብና ከማልማት ባለፈ ለዘመናት የተፈጥሮ ሀብቱን ጠብቆ ያቆመው ህዝብ የሀብቱ ተቋዳሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
እያደገ የመጣው የህዝብ የመልማት ፍላጎት ተጠብቆ የቆየው የተፈጥሮ ሀብት አደጋ ውስጥ በማይከት መንገድ ሊሆን ይገባል ያሉት ዶክተር ኢንጂነር አሥራት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ተፈጥሮ ሀብቱ ሚዛኑን መሳት የለበት ብለዋል። ከዚህም የተነሳ በህብረተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ንብ ማነብ፣እንስሳት እርባታና በሌሎች ተግባራት ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ገንዘብ ድጋፍ ህዝቡ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል ብለዋል። ለዘመናት ተፈጥሮን ጠብቆ ላቆየው ህዝብ እየተደረገ ያለው ስራ በቂ ባለመሆኑ ዘላቂነት ያለው ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዲሁም ክልላችን በተፈጥሮ ጥበቃ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እያለም በአየር ንብረት ተጽዕኖ ስር እንደሚገኝም አንስተዋል። በአከባቢያችን ተጠብቀው ለቆየው ሀብት የሚመጥን የካርቦን ክፊያ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በሀገር ደረጃ በዩኒስኮ ከተመዘገቡት አምስቱ ብዝሃህይወት ቦታዎች ውስጥ ሁለቱ በክልላችን ይገኛሉ። በተጨማሪም ቤንች ሸኮ ዞን የሚገኝ ጥብቅ የደን ሀብትን በተጨማሪነት ለማስመዝገብ በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ ዶ/ር ኢ/ር አስራት አመልክተዋል።
አሁን ላይ ባለው ሂደት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ከኢትዮጵያ ደን ልማት እንዲሁም ከብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በቢሮው አስተባባሪነት ፕሮፖዛል ተዘጋጅቶ የፀደቀ ስሆን ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት የተጠናቀቀ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።
ወደ ካርቦን ክፊያ ለመሄድ አስፈላጊ መረጃዎችን ለማደራጀት ፕሮፖዛል ተዘጋጅቶ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ባሉበት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተከናውኗል ያሉት የቢሮ ኃላፊዉ የመረጃ መሰብሰብ ስራዉ ትልቅ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ በክልላችን የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
ከካርቦንና ከብዝሃ ህይወት ክፍያ የሚገኘው ገንዘብ በምን አግባብ ለማህበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ይደርሳል የሚል ሀሳብ በመያዝ ቢሮዉ የክልሉን የደን ደንብ እና አፈፃፀም መመሪያ አዘጋጅቶ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት አስተችቷል ያሉት ኃላፊዉ የተፈጥሮ ሃብታችን የካርቦን ልቀትን የመምጠጥ መጠኑ ምን ያህል ነው የሚለውን ለማወቅ ሳይንሳዊ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ጊዜያዊ ፍላጎቶችን መሠረት ያደረገ የደን ጭፍጨፋና ወረራ እንዲሁም በባዮስፌር የተመዘገቡ ጥብቅ ደኖችን ላይ ያልተገባ ድርጊት ህዝቡ በመታገል ረገድ እንደጨሁል ጊዜው ትብብሩን እንዲያጠናክር የጠየቁት ዶ/ር ኢ/ር አስራት የክልሉ መንግስት ለዘመናት ህዝቡ ጠብቆ ያቆየውን ሀብት ከተለያዩ አደጋዎች ለመታደግ በትኩረት ይሰራል ሲሉም አንስተዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
