የግብርናን ዘርፍ ለማዘመን ሜካናይዜሽን ዋነኛ መሳሪያ ነው፡፡ በዋናነትም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትና ኢኮኖሚ ለማሻሻል ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡ 

Spread the love

አደጉ የሚባሉት ሀገራት የግብርና ዘርፉን  ያዘመኑት ለሜካናይዜሽን ግብርና ትኩረት በማድረግ ትራክተር እና የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ ሆነዋል፡፡ ስለሆነም የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ያለ ትራክተር እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ፈጽሞ የማይቻል ጉዳይ ነው።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠፊና ለእርሻ አመቺ መሬት ያለ በመሆኑ ይህን መካናይዝድ በሆነ መንገድ በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ከክልሉ አልፎ ሀገሪቱን መመገብ የሚያስችል ምርት የሚገኝበት ነዉ።

ይህን በመገንዘብ በክልሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል መንግስት እና ኅብረተሰቡ በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ ።

አቶ አስራት አሰፋ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ  ናቸዉ። እርሳቸው እንደሚሉት የክልሉ መንግስት ለግብርና ዘርፍ ትኩረት በመስጠት እና ዘርፉን  ለማዘመን ሜካናይዜሽን ዋነኛ መሳሪያ አድርጎ ሰፊ እየሠራ ይገኛል።

አቶ አስራት አክለው የክልሉ መንግስት 37 ትራክቶችን ገዝቶ አገልግሎት ላይ በማዋሉ ጥሩ እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆኑን ገልፀው ቢሮው ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ  ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር በአላጌና አርዳይታል ግብርና ኮሌጆች የክልላችን የመካናይዜሽን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ 50 የሚሆኑ ኦፕሬተሮችና  መካኒክ ባለሙያዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

የግብርና መካናይዜሽን በትራክተር ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችንም በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው በክልሉ የሚገኘውን አንድ የግብርና መካናይዜሽን ማዕከል በመጠቀም ምርጥ ዘር የማባዛት  ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከረጂ ድርጅቶችና ከኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ምርት መሰብሰቢያና መውቂያ ማሽኖችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ በተደረገው እንቅስቃሴ በሞዴል ደረጃ የተሰሩ 10 ሁለገብ ምርት መውቂያ ማሽኖች በክልሉ መሰራጨታቸውን አቶ አስራት አብራርተዋል።

በክልሉ በኮምቫይነር ምርት የማጨድ ልምድ ለማስፋት፣ የደረሱ ምርቶችን በጊዜ ለመስብሰብ እና የዘር ማሳዎችን በኮምቫይነር ለመሸፈን በተደረገው ጥረት በተያዘው የበጀት ዓመት ስድስት ኮምቫይነሮችን በኪራይ በማስመጣት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አቶ አስራት ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *